ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ገበሬዎች አጨቃጫቂ በሆነው የአል-ፋሻጋ አካባቢ ወደ ሱዳን ግዛት ዘልቀው ገብተዋል ሲል የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ሃሙስ ቅሬታን አቀረበ።
በዚሁ የድንበር ዙሪያ የሚኖሩ የሁለቱ ሃገራት ዜጎች በዓል-ፋሸጋ ስር የሚገኝ ሰፊ የእርሻ ቦታ ላይ ለአመታት የቆየ የይገባኛል ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በድንበሩ አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የሱዳን የፀጥታ ሃይሎች በተደጋጋሚ ወደ ይዞታቸው እየመጡ መሬቱ ለሱዳን የተሰጠ ነው በማለት ዕርምጃ ሲወሰድባቸው መቆየቱን ሲገልፁ ቆይተዋል።
በሱዳን የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ለሃገራቸው ከፍተኛ አመራሮች ሪፖርትን ያቀረቡት የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር አዋድ ኢብን ኡፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ወታደሮች በድንበሩ አካባቢ ይዞታቸውን በማስፋፋት ወደ ሱዳን ድንበር ዘልቀው ገብተዋል ማለታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ድንበር ዘልቀው ገብተዋል ቢሉም የተወሰደ ዕርምጃ ይኑር አይኑር ጋዜጣው ያመለከተው ነገር የለም።
250 ኪሎሜርት የሚሸፍነው የአልፋሻጋ የድንበር አካባቢ 600 ሺ ሄክታር ለም መሬት ያለው ሲሆን፣ በድንበሩ ስፍራ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ገበሬዎች አካባቢው ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ ስር መቆየቱን ይገልጻሉ።
በዚሁ ድንበር አዋሳኝ ቦታ በተደጋጋሚ የሚነሳውን ግጭት ተከትሎ የኢትዮጵያና የሱዳን መሪዎች እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 አም ድንበሩን ለማካለል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይሁንና በርካታ ኢትዮጵያውያንና ምሁራን ድንበሩን የማካለሉ ሂደት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ነው በማለት ተቃውሞን ሲያካሄዱ ቆይተዋል።
የሱዳኑ ባለስልጣናት ሁለቱ ሃገራት 1ሺ600 ኪሎሜትር የሚሸፍነውን የድንበር አካባቢያቸውን ለማካለል ስምምነት እንደተደረገ ቢያረጋግጡም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሃገሪቱ ጋር የተደረሰው አዲስ ስምምነት የለም ሲሉ አስተባብለዋል።
ይሁንና ከሃገሪቱ ጋር የተደረገው ስምምነት ከዚሁ በፊት በነበሩ መንግስታት የተደረሰን የድንበር ማካለል ውል ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ግን አስታውቀዋል። የታሪክ ምሁራን በበኩላቸው በኢትዮጵያና ሱዳን መንግስታት መካከል ድንበሩን ለማካለል በቀድሞ መንግስታት የተደረሰ ውል አለመኖሩን ይገልጻሉ።
የሱዳን መንግስት ድንበሩን የማካለሉ ስምምነት መደረሱን ቢያረግግጥም መቼና በምን ሁኔታ ድንበሩ እንደሚካለል እስካሁን ድረስ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ይሁንና በድንበሩ አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ለዘመናት የያዙት ቦታ ለሱዳን የተሰጠ ነው በማለት ወከባን እንደሚፈጽሙባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን ባለፈው ሳምንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በርካታ አዳዲስ ስምምነቶች እንደተደረሰ ቢገልጹም በጋራ ድንበራቸው ጉዳይ ዙሪያ የሰጡት መረጃ የለም።