የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ዕልባት አለመሰጠቱ የአፍሪካ ቀንድን መረጋጋት አደጋ ውስጥ ገብቷል ሲል አውሮፓ ህብረት አስታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2009)

ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው ያለውን የድንበር ግጭት ዕልባት አለመስጠታቸው የአፍሪካ ቀንድን መረጋጋት አደጋ ውስጥ ከቶታል ሲል የአውሮፓ ህብረት ሃሙስ ስጋቱን ገለጠ።

የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የሁለቱ ሃገራት የድንበር ይገባኛል ጥያቄን እልባት ለመስጠት ውሳኔ ያስተላለፈበትን 15ኛ አመት አስመልክቶ መግለጫን ያወጣው ህብረቱ፣ ጉዳዩን የአህጉራዊ ትብብርና ልማትን ለማጠናከር በተያዘው እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አመልክቷል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የዛሬ 15 አመት ብይን ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ አጨቃጫቂ የሆነው አብዛኛው የባድመ አካባቢ በኮሚሽኑ ውሳኔ ለኤርትራ እንዲሰጥ መደረጉ ይታወሳል።

ይሁንና ኢትዮጵያ የድንበር ውሳኔው ፍትሃዊ አይደለም በማለት በፍርድ ቤቱ ብይን ላይ ከኤርትራ ጋር ድርድር እንዲካሄድ ጥያቄን በወቅቱ አቅርባለች።

የኤርትራ መንግስት በበኩሉ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ካልተደረገ ከኢትዮጵያ ጋር በብይኑ ዙሪያ ድርድር እንደሚያደርግ አቋሙን አስታውቋል።

በዚሁ ልዩነት መሰረት ሁለቱ ሃገራት በገለልተኛ አካል የተላለፈን ይግባኝ የሌላውን ውሳኔ ተግባራዊ ሳያደርጉ 15 አመት እንዳስቆጠረ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ አውስቷል።

ይኸው የሁለቱ ሃገራት የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ዕልባት አለማግኘት ከቀጠናው ባሻገር በአለም ሰላምና ደህንነት እንዲሁም በአለም አቀፍ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ ፍርዱን በታዛቢነት ተገኝቶ በፊርማ ማፅደቁን ያወሳው የአውሮፓ ህብረት አክሎ ገልጿል።

ከህብረቱ በተጨማሪ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) የድንበር ኮሚሽን ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ በታዛቢነት በመገኘት ፊርማ ማኖራቸው ይታወሳል።

በቀጠናው ሰላም አለመረጋጋት ስጋት እንደደረሰበት የገለጸው የአውሮፓ ህብረት ሁለቱ ሃገራት ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት ድጋፉን እንደሚያደርግ አክሎ አስታውቋል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፓርላማ ባቀረበው የስድስት ወር ሪፖርት ከኤርትራ ጋር ያለውን አለመግባባት ለመፍታት አዲስ ጥናት መካሄዱን መግለፁም የሚታወስ ነው። ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርትን ያቀረቡት ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ስለ አዲሱ ጥናት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።