ኢህአዴግ “በአገሪቱ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ በጠባብነትና ትምክተኝነት የተነሳ ነው” ሲል ራሱን ሸንግሎ ተሃድሶውን ማጠናቀቁን አስታወቀ

ሚያዝያ ፬ (አራት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያና አማራ እንዲሁም በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች የታዩትን ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተከትሎ አገሪቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስአዋጅ አውጥቶ በወታደራዊ ሃይል እየገዛት ያለው ኢህአዴግ፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ብሎ ያስቀመጠውን ጥልቅ ትሃድሶ ሲያጠናቅቅ፣ ለተቃውሞው መነሻ በውጭ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንን ተጠያቂ አድርጓል። ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶው በድል ተጠናቋል ቢልም ህዝቡ ግን ተሃድሶው የተባለውን ከቁም ነገር አልቆጠረውም።
የኢህአዴግ ምክር ቤት ሁሉንም የምክርቤት አባላት እና ከምክር ቤቱ አባላት ውጭ የሆኑ ሚንስትሮች እና ኤጀንሲ ኃላፊዎችን አካቶ ባደረገው ስብሰባ ፣ በአገሪቱ የታየው ተቃውሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጠባብ እና ትምክህተኛ ሃይሎች በኢህአዴግ ላይ ያደረሱት አደጋ ነው ብሎአል። በኦሮምያ እና አማራ ክልል ተወካዮች የቀረቡለትን የጥልቅ ታሃድሶ ሪፖርት አዳምጦ የችግሮች መጀመሪያ እና መጨረሻ በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረው የብሄርተኛነት ጥያቄ በመሆኑ እሱን መታገል ይገባል በማለት መሰረታዊ የሆነውን የህዝቡን ጥያቄ ዘሎታል።
አማራው በኢሳት እየታገዘ ፣ ኦሮሞው በኦኤምኤን እየተመራ ስርዓቱን ለማፈራረስ ያደረጉት ጥረት ሀገሪቱን ወደ ማጥ ከቷት አልፋል ያለው ኢህአዴግ፣ ይህ እንዳይደገም ልዩ የፖለቲካ ሃላፊነት ለአምባሳደሮች ሰጥቷል። አምባሳደሮች የመገናኛ ብዙሃኑ ህዝባዊ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ከማድረግ ጅምሮ ህግ ፊት በማቅረብ ለማዘጋት ሙከራ ያደርጋሉ።
ኢህአዴግ በመንግስት ሚዲያዎችም ልዩ የፕሮፓጋንዳ ስራ ለመስራት እንዲቻል፣ የኢህአዴግ የፖሮፓጋንዳ ክፍል ከአጀንዳ ቀረፃ እስከ ስርጭት እንዲከታተል ኮሚቴ በይፋ አዋቅሯል፡፡
ወደ አደባባይ የወጣውን ታላቅ ህዝባዊ አመፅ በየደረጃው ባደረግነው ጥልቅ ተሃድሶ ተቆጣጥረነዋል ያለው ምክር ቤቱ፣ የወልቃይትን ጥያቄ አሁን ለመመለስ የሚቻልበት አስቻይ ሁኔታ የለም ሲል በሚቀጥለው አመትም እንኳ ለመፍታት የሚያስችል ብቃት እንደሌለው ፓርቲው ራሱን ገምግሟል፡፡ ነገር ግን በተለመደው የሃሰት ሪፖርት ኢህአዴግ የወልቃይትን ጉዳይ በቅርቡ እንደሚፈታ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ብአዴን በአማራ ክልል የተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ የትምክህት ችግር የፈጠረው ነው በማለት የአማራን ህዝብ በትምክህተኝነት የፈረጀው ሲሆን፣ ኦህዴድ ደግሞ ጠባብተኛነት የፈጠረብኝ ችግር ነው በማለት የኦሮሞን ህዝብ በጅምላ ጠባብ በማለት ፈርጇል።
ዲያስፖራው በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ እያደረሰ ያለው ችግር ለምዕራብ አገራት አምባሳደሮች በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል እንደተነገራቸው ምንጮች ገልጸዋል። ምንም እንኳ ገዢው ፓርቲ ጥልቅ ተሃድሶውን በስኬት እንዳጠናቀቀ ለራሱ ደጋፊዎችና አባላት ቢያስታውቅም፣ ዜጎች ግን መሬት ላይ ያልወረደ፣ በአየር ላይ የቀረ ተሃድሶ ነው በማለት ያጣጥሉታል።
“ከቀበሌ እስከ ክልል ትሃድሶ የለም፣ የኢህአዴግ አመራር ሌባ የሆነበት ምንም ተሃድሶ ያልተካነወነበት ባለትዳር ሳይቀር የሚደፍሩ ናቸው በማለት ዜጎች አስተያየት ይሰጣሉ።