የአውሮፓ ህብረት ካውንስል ጽ/ቤት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ መሆን አለበት ሲል አሳሰበ

ሚያዝያ ፬ (አራት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ15 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ተከትሎ የተነሳውን ጦርነት ለማስቆም የተፈረመውን የአልጀርስ ስምምነት ተከትሎ፣ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን (EEBC) የሰጠው ውሳኔ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ብሎአል።
የአፍሪካ ቀንድን ችግር በዘላቂነት ይፈታል የተባለውን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ተግባራዊ አለመደረጉ እንደሚያሳስባቸው የገለጹት የህብረቱ ካውንስል ጻሃፊ ወ/ሮ ፌዴሪካ ሞጎሪኒ ፣ ችግሩ ከቀጠናው ባለፈም በዓለምአቀፍ ሰላም፣ ንግድ፣ ልማት እና ደህንነት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል። ሁለቱም አገራት ለዘላቂ ሰላም ሲሉ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እና ድንጋጌዎች በማክበር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል ብለዋል ጸሃፊዋ ።
የአውሮፓ ሕብረት በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂነት ያለው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል።