ኢሳት (ሚያዚያ 4 ፥ 2009)
የመንግስት ንግድ ባንኮች በውጭ ሃገር ያሉ ዜጎች ወደ ሃገር ውስጥ ገንዘብን ለሚያስልኩ እስከ መኖሪያ ቤት የደረሰ የዕድል እጣን ለመወዳደሪያነት ማቅረባቸው በግል ባንኮችና በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ዘንድ ቅሬታን አስነሳል።
ንግድ ባንኮች ሰሞኑን የሚከበረውን የፋሲካ በዓልና ሌሎች ጉዳዮችን በማስመልከት ከውጭ ገንዘብ የሚያስልኩ ተወዳዳሪዎችን እስከመኖሪያ ቤት የሚደርስ ሽልማት ለመስጠት ሰፊ የማስታወቂያ ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑ ታውቋል። ይሁንና መንግስታዊ ባንኮች እያካሄዱ ያለው ዘመቻ ከሃገሪቱ የምንዛሪ ተመን አሰራር ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስታውቀዋል።
የህብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ የንግድ ባንኮች አሰራር ፍትሃዊ ያልሆነ የገበያ ውድድርን እያስከተለ እንደሆነ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
አንድ ግለሰብ ከመኪና ዋጋ በታች የውጭ ምንዛሪ ተልኮለት መኪና በእጣ ቢደርሰው፣ ይህ መኪና ከውጭ ምንዛሪው ተመን በላይ ባንኩ እየከፈለው ስለሆነ አሰራሩ ከህጉ ጋር የማይሄድ መሆኑን አስረድተዋል።
ለውጭ ምንዛሪ አስመጪዎች ሽልማት መስጠት በአንዱ ባንክ በኩል ሲመጣ የነበረውን ምንዛሪ በሌላ ባንክ ሊያደርግ ይችል ይሆናል እንጂ እንደ ሃገር የውጭ ምንዛሪን ይጨምራል ብለው እንደማያምኑ የባንክ ባለሙያው ገልጸዋል።
ንግድ ባንኮች የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ላኪ ነጋዴዎችን ማበረታታትና አገልግሎቱን ማቀላጠፍ ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ እንደሚሆን አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ አክለው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር እና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚደንት አቶ አዲሱ ሃባ በበኩላቸው ከመኪና እስከ መኖሪያ ቤት የደረሰው የባንኮች የመወዳደሪያ አካሄድ አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳት እንዳለውና በተለይም አነስተኛ ቅርንጫፍ ያላቸው ባንኮች የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባንኮቹ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ለማሳደግ የአሁኑ አይነት ውድድር ውስጥ ከሚገቡ ይልቅ አገልግሎታቸው ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ እንደሚሆን አቶ አዲሱ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክንትል ገዢ አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ ባንኮች የውጭ ምንዛሪን በራሳቸው በኩል ለማስላክ እያደረጉት ያለው ነገር ፍትሃዊ ያልሆነ የገበያ ውድድር ስለማስከተሉ የደርሰን ቅሬታ የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥዋል።
ይሁንና ባንኩ መሰል ቅሬታ ከቀረበለት ጉዳዩን የሚያጤነው ይሆናል በማለት በቅሬታው ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በመድረስ ከሃገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢ በላይ መድረሱን ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና የንግድ ባንኮች በተለያዩ ጊዜያት የተጋነነ ሽልማትን በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በብቸኝነት ለመቀበል ያያዙት አካሄድ ፍትሃዊ አለመሆኑንና የግል ባንኮችን ተወዳዳሪነት የሚጎዳ ነው ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።