ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንዔል ሽበሺ ፍርድ ቤት ሊቀርቡም ሆነ ሊለቀቁ እንደማይችሉ እንደተገለጸላቸው ተናገሩ

ኢሳት (ሚያዚያ 4 ፥ 2009)

በቦሌ ክፍለ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንዔል ሽበሺ የእስር ቤቱ አመራሮች ፍርድ ቤት ሊያቀርቧቸውም ሆነ ሊለቋቸው እንደማይችሉ እንደገለጹላቸው ከእስር ቤት ባስተላለፉት መልዕክት አስታወቁ።

ላለፉት አምስት ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀቡና ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ጉዳያችሁ ከአቅማችን በላይ ነው ሲሉ ሰሞኑን ምላሽ እንደሰጧቸው አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ታሳሪዎቹ የጻፉትን ደብዳቤ በማስደገፍ ዘግቧል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ሊያቆዩአቸው እንደማችይሉ የገለጹላቸው የእስር ቤቱ ሃላፊዎች፣ ሁለቱ ታሳሪዎችን ለማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት ለማስረከብ ቢወስዷቸውም የማዕከላዊ ሃላፊዎች አንቀበላቸውም እንዳሏቸው ታውቋል።

የሁለቱ ታሳሪዎች ጉዳይ በምን ሁኔታ መታየት እንዳለበት ግራ የተጋቡ የቦሌ ክፍለ ከተማ እስር ቤት አመራሮች ተጠርጣሪዎች ልደታ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ቢሮ እንደወሰዷቸው መጽሄቱ በዘገባው አመልክቷል።

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና አቶ ዳንዔል ሽበሺ ወደ አቃቤ ህግ ቢሮ መወሰዳቸውን ተከትሎ ፖሊስ ሁለቱ ታሳሪዎች በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ የተወሰደባቸው የእጅ ስልክ ለተጠረጠሩበት ወንጀል ማስረጃ ብሎ አቅርቧል።

ፖሊስ ለከሳሽ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ማስረጃ ምክንያት በማድረግ ሁለቱ ታሳሪዎች ጉዳያችሁ ከአቅሜ በላይ ሆኗል ወዳለው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው እስር ቤት ተመልሰው እንደሚገቡ ማድረጉ ተመልክቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣትን ተከትሎ ሁለቱ ታሳሪዎች ከጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ጋር በማህበራዊ ድረገጾች ባሰፈሯቸው ፎቶዎችና የተለያዩ አስተያየቶች በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ይሁንና ከመካከላቸው ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ በነጻ የተሰናበተ ሲሆን፣ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ያለምንም ክስ ለአምስት ወር በእስር ላይ ይገኛሉ።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ መላቀቅም ሆነ በሁለቱ ታሳሪዎች ጉዳዮች የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ሶስቱ ታሳሪዎች በእስር ላይ እያሉ በእስር ቤት ሃላፊዎች በደል ይደርስባቸው እንደነበር ሲገልጹ ቆይተዋል።

የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንዔል ሺበሺና ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለእስር ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣትን ተከትሎ ከ24 ሺ የሚበልጡ ሰዎች ለእስር ተዳርገው የነበረ ሲሆን፣ ወደ አምስት ሺ አካባቢ የሚጠጉ ክስ እንደሚመሰርትባቸው ተገልጿል።

ሆኖም ታሳሪዎቹ ለእስር ከተዳረጉ ወራቶች ቢቆጠሩም ክሱ መቼ እንደሚመሰርትባቸው የታወቀ ነገር የለም።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የአዋጁን መውጣት ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የጅምላ እስራት በመፈጸም ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የአውሮፓ ህብረት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ የበርካታ ሰዎች እስር መቀጠሉ ስጋት እንዳደረሰበት መገልጹም ይታወሳል።