ኢሳት (ሚያዚያ 4 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በመባባስ ላይ ያለውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ በበርካታ ወረዳዎች የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረቡዕ ይፋ አደረገ።
ድርጅቱ በበሽታው ምን ያህል ሰዎች እስካሁን ድረስ ህይወታቸው እንዳለፈ ከመግለጽ ቢቆጠብም፣ ወረርሽኙ በትንሹ በ40 ወረዳዎች ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ከ300 በላይ የጤና ባለሙያዎች በክልሉ በሽታውን ለመቆጣጠር በቅርቡ ቢሰማሩም የበሽታው ወረርሽኝ ስርጭቱ ሊገታ አለመቻሉ ታውቋል። አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በሶማሌ ክልል በመባባስ ላይ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ አስከፊነት ድረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን አስታውቀዋል።
በ40 ወረዳዎች ውስጥ በየዕለቱ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች መኖራቸውን የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በባቢሌ የሚገኘው ጊዜያዊ የተፈናቃዮች መጠለያ በወረርሽኙ መጠቃቱን አመልክቷል።
የወረርሽኙ መዛመትን በሰው ህይወት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ተከትሎ የወረርሽኙን መዛመት ለመቆጣጠር የተመደቡ ሰራተኞች ቁጥር ወደ አንድ ሺ ከፍ እንዲል መደረጉም ታውቋል።
በአካባቢው ከፍተኛ የውሃ እጥረት መከሰቱ የንፅህና አጠባበቅ ችግርን በመፍጠር የበሽታው ወረርሽን በቀላሉ እንዲሰራጭ አስተዋጽዖ ማድረጉም ተመልክቷል።
ባለፈው ወር የካቶሊክ እርዳታ ተቋም ተወካዮች የተበከለ የግድብ ውሃን የተጠቀሙ ስድስት ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ ነዋሪዎች ደግሞ ለህክምና መዳረጋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ እንዲጋለጡ ማድረጉ ይታወቃል።
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርቁን ለመከላከል እየሰጠ ያለው ምላሽ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ በመሄድ ላይ ሲሆን በተለይ በሶማሌ ክልል ችግሩ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊሸጋጋር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ርብርብ እየተደረግ ነው ቢሉም፣ የድርቁ አደጋ ለሰዎች ሞት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አድርጓል።
ከባለፈው ወር ጀምሮ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች መጣል የነበረበት የበልግ ዝናብ በሚፈለገው መጠን ባለመገኘቱ የድርቁ አደጋ እየተባባሰና እስከቀጣዩ አመት ዘላቂ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።
መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቁን ለመከላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይተዋል። ይሁንና በእስካሁኑ ቆይታ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ ከተጠበቀው በታች መሆኑ ተገልጿል።