“የመንግስት ጣልቃ ገብነት ሊቆም ይገባል” ሲል የዋድላ ወረዳ ቤ/ክህነት አስታወቀ

ሚያዝያ ፫ (ሦስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ቤተ ክርስቲያን የራሱዋ የሆነ መተዳዳሪያ ደንብ ያላት ቢሆንም፣ አገዛዙ በየጊዜው ጣልቃ እየገባ መመሪያዋን ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉዋን የወረዳው ቤ/ክህነት ሃላፊዎች አቤቱታ አሰምተዋል።
አመራሮቹ ፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ጠዋት ወደ ቤ/ክርስቲያን እየመጡ “ ስብሰባ አለ፣ መልዕክት አለ፣ ይህን ክፍያ ክፈሉ” እያሉ መእመናንን እያስቸገሩ ነው ያሉ ሲሆን ፣ አሰራሩ ቤ/ክርስቲያኑዋ የሰበሰበቻቸውን ምዕመን ለመበተን የተደረገ አሰራር ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። ገዢው ፓርቲ ይህንን አሰራር ካላቆመ ቤተ/ክርስቲያኑዋ ሃዋሪያዊ ተልዕኮዋን የማትወጣበት ደረጃ ትደርሳለች ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የቤ/ክርስቲያኑዋ አመራሮች የሚሰጡት ውሳኔ በየጊዜው በገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እንደሚነቀፍ የሚገልጹት የወረዳው የቤተ ክህነት አመራሮች፣ ድርጊቱ በሙሉ የቤ/ክርስቲያኑዋን አስተዳደራዊ ስርዓት ለመናድ የሚደረግ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ህገመንግስት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ መሆናቸው ሰፍሮ ቢገኝም፣ ገዢው ፓርቲ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደህንነት መዋቅሩን ዘርግቶ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል። የሃይማኖት አባቶች ያለ ኢህአዴግ እውቅና መሪዎቻቸውን በነጻነት መምረጥ አይችሉም። ይህንን አሰራር የተቃወሙ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን አባቶችና የሙስሊም ኢትዮጵያውያን መሪዎች፣ ለእስር፣ ለስደትና ለእንግልት ተዳርገዋል።
ተመሳሳይ ጥያቄ ባቀረቡት የዋድላ ደላንታ የቤተክህነት መሪዎችም ላይ ገዢው ፓርቲ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።