አርበኞች ግንቦት7 ተጨማሪ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ

ሚያዝያ ፪ (ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈጸሙን የሚገልጸው አርበኞች ግንቦት7 ፣ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓም ከሱዳን ተነስቶ ወደ ጎንደር በማቅናት ላይ የነበረ የሱዳን ታርጋ ያለው መኪና ላይ በፈጸመው ጥቃት የመኪናውን ከፊል አካል ማቃጠሉን ገልጿል። ጥቃቱ የተፈጸመው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ካለበት አካባቢ ነው።
እንዲሁም ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓም አምባጊዮርጊስ አካባቢ የአገዛዙ ሰላይ ነበር ባለው እንዳልከው ንጉሴ በተባለ ግለሰብ ላይ እርምጃ እንደወሰደበት ንቅናቄው ለኢሳት በላከው መረጃ አስታውቋል።
ንቅናቄው ሁለገብ የትግል ስልቱን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ የህዝባዊ ጥሪ ወረቀቶች ከሰሜን አልፈው በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች በትኗል። ኢሳት ወረቀቶች መበተናቸውን ከስፍራው ከሚገኙ ወኪሎቹ ለማረጋገጥ ችሎአል። የወረቀቶችን መበተን ተከትሎ በርካታ ዜጎች፣ ታፍሰው ምርምራ እየተካሄደባቸው ነው።
የኢህአዴግ ፓርላማ በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ ለአዋጁ መራዘም የሰጡት ምክንያት በክልል ድንበሮች አካባቢ ተቃውሞች መኖራቸውና ያልተያዙ አመራሮች አሉ የሚል ነው።
ምንም እንኳ ገዢው ፓርቲ በይፋ የሚደረጉ ተቃውሞችን ለማፈን ቢችልም፣ በስውር የሚደረጉ ተቃውሞዎች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ነው።