ኦብነግ ከሶማሊ ልዩ ሃይልና ከመከላከያ ጋር መዋጋቱ ተዘገበ

ሚያዝያ ፪ (ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኦጋዴን ኒውስ ኤጀንሲ እንደዘገበው ከሁለት ቀናት በፊት በመከላከያ ሰራዊት በሚደገፈው የሶማሊ ልዩ ሃይልና በኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት መካከል በደጋሃቡር አውራጃ፣ በብርቆት ወረዳ ልዩ ስሙ ሊዲለይ በሚባል ስፍራ ላይ በተደረገ ውጊያ 3 አዛዦችን ጨምሮ 17 ወታደሮች መገደላቸውን የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል። 21 ቁስለኛ ወታደሮች ደግሞ በአየር ወደ ጅግጅጋ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የአይን እማኞች እንደገለጹለት የዜና ድርጅቱ አስታውቋል።
የኦብነግ ወታደሮች በኮሌራ በሽታ ለተጠቁት የአካባቢው ሰዎች መድሃኒት በማከፋፈል ላይ እያሉ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የዘገበ ሲሆን፣ በኦብነግ በኩል የደረሰ ጉዳት የለም ተብሎአል። ይህንኑ ተከትሎ የአገዛዙ ወታደሮች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑም ተዘግቧል። ጥቃቱን በተመለከተ በክልሉ መንግስት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።