ኢሳት (ሚያዚያ 2 ፥ 2009)
የማላዊ ፖሊስ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ 56 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሰኞ ገለጸ።
በየወሩ በሃገሪቱ ለእስር የሚዳረጉ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑንና ድርጊቱ አሳሳቢ መሆኑን የማላዊ ኢሚግሬሽን ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።
56ቱ ኢትዮጵያውያን ካሮንጋ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ መዳረሻቸው ወደ አልታወቀ ቦታ በጭነት ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እንዳሉ በጸጥታ ሃይሎች መያዛቸውን ማላዊ 24 የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑን የያዘውን ተሽከርካሪ ለማስቆም ፖሊስ ጥረት ባደረገ ጊዜ ማንነቱ ለጊዜው ያልታወቀ ሹፌር ተሽከርካሪውን አቁሞ መሰወሩም ተመልክቷል።
የማላዊ ፖሊስ ማንነቱ ያልታወቀውን ሹፌር በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆኑ ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ምዙዙ ተብሎ በሚጠራ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።
ሰደተኞቹ ያለምንም የጉዞ ሰነድ ወደ ሃገሪቱ በመግባታቸው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው አመት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከ100 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሰብዓዊ አያያዝ በጎደለው ሁኔታ በእስር ቤቶች ይገኛሉ በማለት ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ዘመቻ ከፍተው እንደነበር ይታወሳል።
የማላዊ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች በበኩላቸው በእንግልት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በጀት አለመኖሩን ገልጿል። የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በሶስት እስር ቤቶች የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ከምግብ እጥረትና ከመሰረታዊ ንፅህና አቅርቦት አለመኖር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የጤና እክል እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ሲገልፅ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት የስደተኛ ድርጅቱ ኢትዮጵያውያን ሰደተኞቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ የገንዘብ ድጋፍ እያፈላለገ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
በእስር ቤት የሚገኙ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የተላለፈባቸውን የዘጠኝ ወር እስራት ቢያጠናቅቁም ለሁለት አመት ያህል በእስር ላይ መቆየታቸውን የማላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይገልጻሉ። በርካታ ኢትዮጵያውያን ማላዊን ለመሸጋገሪያነት በመጠቀም ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ጥረት እንደሚያደርጉ ለመረዳት ተችሏል።
በማላዊ እስር ቤት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልታወቀ በርካታ ኢትዮጵያውያን በታኒዛኒያ እና በጎረቤት ሃገራት እስር ቤቶች እንደሚገኙም የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከሃገሪቱ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የስደተኛ ምርጃ ድርጅቶች ይገልጻሉ።