በወህኒ ቤት ሰቆቃ እየፈጸሙ ያሉት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 2 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ከ90 በመቶ በላይ በትግራይ ተወላጆች ቁጥጥር ስር መውደቁን፣ በወህኒ ቤቱ ሰቆቃ የሚፈጽሙት በተመሳሳይ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን አቶ ሃብታሙ አያሌው ገለጸ።

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረውና ከአንድ አመት በላይ በወህኒ ቤት ያሳለፈው አቶ ሃብታሙ አያሌው ይህንኑ የተናገረው በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ በተዘጋጀ መድረክ ላይ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

በቨርጂኒያ አርሊንግተን ከተማ ሼራተን ሆቴል ዕሁድ ሚያዚያ 1 ፥ 2009 አም በተዘጋጀው መድረክ አቶ ሃብታሙ አያሌው ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ በሃገሪቱ ውስጥ ያለን ሰቆቃ በዝርዝር ገልጿል።

ለጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ በመጠየቅ ንግግሩን የጀመረው ሃብታሙ አያሌው የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ችግሮች በማስረጃ እየነቀሰ በጥልቀት ተመልክቷል። ከ90 በመቶ በላይ የፍትህ ስርዓቱ በህወሃት አባላት ቁጥጥር ስር መውደቁን የገለጸው የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው በእስር ቤቶች ሰቆቃ የሚፈጽሙትም በአብዛኞቹ በተመሳሳይ ከአንድ አካባቢ የመጡ የህወሃት አባላት መሆናቸውንም ዘርዝሯል።

እነዚህ ወገኖች በሌላው ላይ የሚፈጽሙትን መጠነ ሰፊ ሰቆቃ በራሳቸው በትግራይ ተወላጆች ላይ ጭምር የሚፈጽሙበትን አጋጣሚ መኖሩንም፣ አፈወርቂ የተባለ የትግራይ አዲዳሮ ተወላጅ ላይ የተከሰተን አጋጣሚ አስታውሷል።

የቀድሞ የአዲስ አበባ የደህንነት ሃላፊ የህወሃት አባል አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካዔል በእስር ቤት ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው ቆመው ያስገረፉት የጠ/ሚ/ሩ የማህበራዊ ጸጥታ አማካሪ ጸጋዬ በርኼ እንደነበሩም ተገልጿል።