ኢሳት (ሚያዚያ 2 ፥ 2009)
የሌተናል ጄነራል ጃጋማ ኬሎ የቀብር ስነስርዓት ትናንት ዕሁድ በቅድስተ-ስላሴ ቤ/ክርስቲያን በርካታ ሰዎች በተገኙበት ተፈጸመ።
በጣሊያን የወረራ ጦር ጊዜ ባደረጓቸው ትግሎች በርካታ ድሎች መጎናጸፋቸው የሚነገርላቸው ሌተናል ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ባደረባቸው ህመም ሳቢያ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ በ96 አመታቸው ባለፈው አርብ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።
እሁድ በተከናወነው የቀብር ስነ-ስርዓት የቤተሰብ አባላት እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናትና የኢትዮጵያ አርበኞች መታደማቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
“የበጋው መብረቅ” በሚል የትግል መጠሪያ የሚታወቁት ጀኔራል ጃጋማ በወጣት እድሜያቸው ከቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር በመሆን በአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት በርካታ አኩሪ ድሎችን እንዲቀናጁ የህይወት ታሪካቸው ይገልጻል።
የጣሊያን ወረራ ከከሸፈ በኋላ ሃገራቸውን በውትድርና ሲያገለግሎ የቆዩ ሲሆን፣ ለሃገራቸው ላበረከቱት አስተዋፅዖም በተለያዩ ጊዜያት የብሄራዊና ሌሎች ሽልማቶች ሲሰጧቸው ቆይተዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባትና ሜጫ አውራጃ ዩብዲ ወረዳ የተወለዱት ጀኔራል ጃጋማ ባለ-ትዳርና ስድስት ልጆች አባት እንደነበሩም ታውቋል።