በምስራቅ ጉጂ በረሃብና በበሽታ ህጻናት እያለቁ ነው ተባለ

ሚያዝያ ፩ (አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት በኦሮምያ ክልል በምስራቅ ጉጂ ዞን ቆላ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ መግባቱንና ይህንን ተከትሎም ወረርሽኝ በመከሰቱ የበርካታ ህጻናት ህይወት እያለፈ ነው ። በተለይ በዞኑ በሚገኙ 6 ወረዳዎች የሚላስ የሚቀመስ የለም የሚሉት ነዋሪዎች፣ ህጻናት በተቅማጥና ትውከት እያለቁ ነው ይላሉ።
በሃራቀሎ፣ ሉባን፣ ሰባ ቦሩ እና ደዋ ቀበሌ የሚኖሩ ነዋሪዎች የሚደርስላቸው አካል በመጥፋቱ ከፍተኛ አደጋ አንዣቦባቸዋል። የገጠሩም የከተማውም ህዝብ ያለችውን ምርት ለመግዛት እየተሻማ መሆኑ፣ ሁኔታውን አስፈሪ አድርጎታል ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ከህጻናት በተጨማሪ በርካታ የቤት እንስሳት ማለቃቸውንም ተናግረዋል። በከተሞች ደግሞ ስኳርና ዘይት በመጥፋቱ ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል።