ሚያዝያ ፩ (አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪዎች ለኢሳት በላኩት መረጃ በሐዋሳ ፣ በወላይታ ከተማ ፣ በአርባምንጭ ፣ በኮንሶ ፣ በጅንካ እንዲሁም በአቶ ኃ/ማሪያም ደሰላኝ የትውልድ አከባቢ በሆነው አረካ አካባቢ “ ከአሁን በሁዋላ በወያኔ መታለል ይቁም፣ የታጋይ አርበኞቻችን ደም በከንቱ እንደፈሰሰ አይቀርም፣ በወያኔ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝቡን መብት ለማፈን እና አርበኞችን ትግል ለማደናቀፍ ያለመ ቢሆንም የአርበኞች ትግል አይደናቀፍም፣ ከባርነት መውጫ ጊዜው አሁን ነው” የሚሉና ሌሎችም በርካታ መፈክሮችን በግድግዳዎች፣ በመስሪያ ቤት በሮችና በኤሌክትሪክ ምሰሰዎች ላይ መለጠፋቸውን በፎቶ ግራፎች አስደግፈው ያለኩት መረጃ ያመለክታል።
ከጂንካ ከሰአት በሁዋላ በደረሰን ዜና ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7 ወረቀት መበተኑን ተከትሎ የህወኃት/ ኢህአዴግ አገዛዝ የከተማዋን ነዋሪዎች እያመሰ ይገኛል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት ድርጊቱን ተከትሎ አምስት የከተማዋ ነዋሪዎች በጥርጣሬ እየተፈለጉ እንደሆነ ታውቋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሰረት ይህንኑ ወረቀት ለጥፈዋል ተብለው ከሚፈለጉት ተጠርጣሪዎች ሦስቱ ማለትም — 1ኛ/ መምህር ዓለማዬሁ መኮንን — የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊበ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ምክትል ሊቀመንበር ፤2ኛ/ ወጣት ዳዊት ታመነ — የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ የዞን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና 3ኛ/ አቶ ስለሺ ጌታቸው –የከተማዋ ነዋሪ ዛሬ ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት ላይ ዞኑ ፖሊስ መምሪያ ቀርበው የእጅ አሻራ ሰጥተው መመለሳቸው ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ሦስቱም ተጠርጣሪዎች -ከዚህ በፊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባልዋሉበትና በማያውቁት ጉዳይ ተጠርጥረው ከሦስት ወር እስከ አራት ወር ያለስንቅ በዞኑ ፖሊስ መምሪያ ታስረው በነጻና በዋስ የተፈቱ ናቸው።
ይህንን የህዝብ ግምት በሚመለከት ያነጋገርናቸው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊበ ኅብረት /ኦህዲኅ/ አመራር ‹‹ ህወኃት/ኢህአዴግ በጨነቀው ቁጥር እንዲህ ዓይነቱን የማስፈራሪያ እርምጃ በመውሰድ ህዝብን ለማፈን የሚደረግ የተለመደ ሴራ መሆኑን አመራሩ፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው የዞኑ ነዋሪ የተረዳው ስለሆነ እያደረጉ ያሉት ከንቱ ድካም ነው፡፡ ህዝቡ እነርሱ የሚያስቡትን ቀድሞና አልፎ ሄዷል፣ ይህን መረዳት ስላልቻሉ የሚያደርጉት ነውና እነርሱ ይሰለቻቸው እንደሆን እንጂ እኛ በእነርሱ ግፊትና ጫና ተማረን የምንሄድበት/የምንሰደድበት ምክንያት የለም፡፡ ይልቁንም በሰላማዊ ትግላችን እንድንጸና ያጠነክረናል፡፡›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል ንቅናቄው በጎንደር በህወሃት/ኢህአዴግ ደጋፈዎች እና የአካባቢ መሪዎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት መቀጠሉን ገልጾ፣ የዚሁ እርምጃ አካል የሆነ ሚያዝያ 01 ለ 02 አጥቢያ ከሌሊቱ 7፡00 ላይ በደቡብ ጎንደር ዞን የሊቦ ከምከም ወረዳ አዲስ ዘመን ከተማ በሚገኘው አስተዳደር ፅ/ቤት ላይ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል። በመስተዳድሩ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን በመግልጽ ዝርዝር መረጃ አለሰጠም።