መሬታቸውን የተነጠቁ አርሶአደሮች ካሳ ሳይከፈላቸው ለአመታት መቆየታቸውን ገለጹ

ሚያዝያ ፩ (አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአዋሽ ሐራ ገበያ – መቀሌ እየተገነባ ካለው የባቡር መስመር ጋር ተያይዞ አርሶአደሮች ያላ አንዳች የካሳ ክፍያ ለዓመታት መቆየታቸውን ተናገሩ፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳን አቋርጦ ወደ መቀሌ ከተማ እየተገነባ ያለው የባቡር መስመር በርካታ አርሶአደሮችን ለችግር ዳርጐ መቆየቱን የቀበሌ ነዋሪዎች ለመንግስት ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በባቡር ሃዲዱ ግንባታ ምክንያት መሬታቸው የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች ለሁለት ዓመት ያህል ካሳ ሳይከፈላቸው ቆይቷል፤ ቆይቶ የተከፈላቸውም ቢሆን በቂ አከመሆኑን አርሶአደሮች ይናገራሉ፡አርሶአደሮች “መሬታችን በትክክል ተለክቶ በካሬ ሜትር ማግኘት የሚገባንን ክፍያ አላገኘንም” እንደሚሉ የአካባቢው አመራሮች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የራያ ቆቦ ወረዳን ጨምሮ ሌሎች የባቡር መስመሩ አቋርጧቸው የሚያልፉ ወረዳዎች የበልግና የመኽር ምርት አብቃይ መሆናቸው እየታወቀ የበልግ ምርታቸው የካሳ ክፍያ ስሌት ውስጥ አልገባላቸውም።
መሬት ለገረ ጋንቲና ለሌሎች ለባቡር መንገዱ ግንባታ ለሚውሉ ግብአቶች ማምረቻ ተወስዶባቸው መሬታቸው ግንባታው ሲጠናቀቅ ለእርሻ ተግባር እንደማይውል እየታወቀ ዘላቂ የካሳ ክፍያ አለመፈጸሙም በአርሶአደሮች ዘንድ ቀሬታ ፈጥሯል፡፡
ምንም እንኳን ከአዋሽ ሐራ ገበያ – መቀሌ የሚል የፕሮጀት ስም ለባቡሩ ሃዲድ ግንባታ ቢሰጠውም በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች አብዛኛውን ወደጎን አድርጎ ማለፉ በንግድ ትስስሩ ሂደት እንዲጠቀሙበት የታሰበው ለትግራይ ክልል ነጋዴዎች ብቻ ነው በሚል ሰፊ ቅሬታ ፈጥሯል።