ሚያዝያ ፩ (አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሕገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ ገብተዋል የተባሉ 56 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በማላዊ የድንበር ፖሊሶች መያዛቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ። ለጊዜው መነሻቸው ከየት እንደሆነ ያልታወቀው ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በመኪና ተጭነው በሕገወጥ መንገድ ወደ ካሮንጋ ግዛት ሲያቀኑ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ሃምሳ ስድስቱም ኢትዮዮጵያዊያን ስደተኞች በሙሉ ወንዶች መሆናቸውን እና የጭነት መኪናው አሽከርካሪ መኪናውን በመተው ከአካባቢው መሰወረኑን ፓሊስ ገልጿል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ካለምንም ሕጋዊ ቪዛ ማላዊ መግባታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የስደተኞች ሕግ አንቀጽ 21 ንኡስ አንቀጽ 1 መሰረት ክስ ይመሰረትባቸዋል። ኢትዮጵያዊያኑ በአሁኑ ወቅት በሙዙዙ እስር ቤት ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ የማላዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ገዥው ፓርቲ ህወሃት ኢህአዴግ ሁለት አሃዝ ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ አምጥቻለው እያለ በመገናኛ ብዙሃን ቢዘግብም ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ግን አገራቸውን ጥለው ሕይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ በአርቱም ማእዘናት መፍለሳቸውን አላቋረጡም።