በሽብርተኛ ወንጀል ክስ ነጻ የተሰናበቱት ሁለት ጦማሪያን በአዲስ ወንጀል ክስ እንዲከሰሱ የተላለፈው ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግ ሲፒጄ ጠየቀ

ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2009)

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሽብርተኛ ወንጀል ክስ ነጻ የተሰናበቱት ሁለት ጦማሪያን በአዲስ ወንጀል ክስ እንዲከሰሱ ያስተላለፈው ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጠየቁ።

የታችኛው ፍርድ ቤት ባለፈው አመት የሽብርተኛ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ጦማሪያን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ከሳሽ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ፍርድ በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል።

በዚሁ ይግባኝ ላይ ብይን የሰጠው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጦማሪያኑ አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናዔል ፈለቀ ሁከትን ማነሳሳት በሚል አዲስ ክስ እንደተመሰረተባቸው ሃሙስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ይሁንና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው CPJ (ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ) በሁለቱ ጦማሪያን ላይ የተላለፈው ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ተከሳሾቹ በነጻ እንዲሰናበቱ ጠይቋል።

በድርጅቱ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አንጀላ ኬንታል የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተገቢ የሆነ ስራ በመስራት የተከሳሾችን መብት እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

አምነስቲ ኢንተናሽናል በበኩሉ ሃሳብቸውን በተለያዩ መንገዶች በመግለጻቸው ምክንያት ዳግም ክስ የተመሰረባቸውን ሁለቱ ጦማሪያን የፍትህ መጓደል ማሳያ ናቸው ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።

ጦማሪያኑ ሃሳባቸው በፅሁፍ የመግለጻቸው መብት በኢትዮጵያ ህግ ጭምር የተከበረ ቢሆንም፣ እየቀረበባቸው ያለው ክስ ምክንያታዊ አይደለም ሲሉ የድርጅቱ የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሙቶኒ ዋንየኪ ገልጸዋል።

መንግስት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን ለእስር በዳረገ ጊዜ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ዕርምጃው ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ ላይ የተከፈተ ዘመቻ ነው ሲሉ ተቃውሞ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው አመት በሃገር ውስጥ የነበሩት ጦማሪያን ከተመሰረተባቸው ክስ በነጻ እንዲሰናበቱ ቢያደርግም ጦማሪያኑ ከሃገር እንዳይወጡና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ መቆየቱን ሲገልፁ ቆይተዋል።

በአራት ጦማሪያን ላይ የቀረበን የይግባኝ ጥያቄ ሲመለከት የቆየው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሳሽ አቃቤ ህግ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ሁከትን አነሳስተዋል የሚል ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ማቅረቡን ገልጸዋል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ጦማሪያኑን በሽብርተኛ ወንጀል ለመክሰስ የሚያስች በቂ ማስረጃ እንዳላቀረበ በታችኛው ፍርድ ቤት ተሰጥቶ እንደነበር ውሳኔ ጋር ተመሳሳይ ብይን አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ ሁለት ጦማሪያን በተመሳሳይ ሁኔታ በነጻ እንዲሰናበቱ መወሰኑም ታውቋል።