ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2009)
ኢትዮጵያን ከጠላት የጣሊያን ወራሪ ጦር የተከላከሉት ታዋቂው አርበኛ ሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
ከ15 አመት ለጋ እድሚያቸው ጀምሮ ጫካ በመግባት የጣሊያንን ጦር ያርበደበዱት ጀግናው ሌተናል ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ በአጼ ሃይለ-ስላሴ ዘመን የጦር አዛዥ እስከመሆን ደርሰዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሸዋ ጊንጪ አቅራቢያ በጅባትና ሜጫ አውራጃ በዳንዲ ወረዳ ዩብዶ በሚባል ቦታ የተወለዱት ሌተናል ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ በ96 አመት ዕድሜያቸው በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ መጋቢት 29 ፥ 2009 በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሌተናል ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ ንጉስ ሃይለ-ስላሴ በስደት እንግሊዝ በነበሩበት ጊዜ የራሳቸውን ጦር በማደራጀት ኢትዮጵያን ከወራሪው ጣሊያን በመከላከል ወደር የሌለው ጀብዱ ፈጽመዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን ወራሪዎች የማረኩትና የገደሉት ሌተናል ጀኔራል ጀጋማ ኬሎ፣ አጼ ሃይለስላሴ ከእንግሊዝ ከተመለሱ በኋላ የወርቅ ሰዓትና ገበርዲን ካባ ተሸልመዋል። በርካታ የሜዳሊና ኒሻን ተሸላሚም ናቸው። ለሃገራቸው ኢትዮጵያ የጋለ ፍቅር የነበራቸው ሌተናል ጀጋማ ኬሎ የ 1 ወንድና የአራት ሴት ልጆች አባት እንዲሁም የልጅ ልጆችን ለማየት የታደሉ አያት ነበሩ።