በአዲስ አበባ ቤት የማፍረስ ዘመቻው ተባብሶ ቀጥሏል ከ20 ሽህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ

መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አካባቢ ያሉ ነባር ባለይዞታ ነዋሪዎች ካለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀሉ ተባብሶ ቀጥሏል። ለዘመናት ተወልደው ያደጉበት መኖሪያ ቤት፣ የሸቀጥ ማከፋፈያ ሱቆች፣ ስጋ ቤቶች፣ ፋርማሲዎች፣ ግሮሰሪዎች፣ የተለያዩ አነስተኛ እና የጅምላ ማከፋፈያ የንግድ ድርጅቶች በዘመቻ እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው።
በቀበሌ ቤቶች ውስጥ ነዋሪ ለሆኑት ለ6 ወራት የቤት ኪራይ የሚሆን 30 ሺህ ብር፣ ለእቃ መጓጓዣ 12 ሺህ ብር በድምሩ 42 ሺህ ብር የተሰጣቸው ሲሆን ተከራይተው እና በቤተሰባቸው ግቢ ውስጥ ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩ ቤተሰቦች ግን ምንም ዓይነት ካሳ ሳይሰጣቸው እንዲባረሩ ተደርገዋል። ማረፊያ በማጣት ወዳጅ ዘመድ የሌላቸው ኮንዶሚኒየም የመክፈል አቅሙን ያጡት ድሃ ነዋሪዎች በቀበሌ ግቢ ውስጥ በሚገኙ አዳራሾች፣ በድንኳኖች እና በጎዳና ላይ ለመጠለል ተገደዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ይዘው ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን በምሬት ይናገራሉ።
ከአፍሪካ ህብረት ፊትለፊት የሚገኙ መኖሪያ እና የንግድ ቤቶች፣ በተለምዶ ወላሞ ሰፈር የሚባለው እና የድሮ በግ ተራን ጨምሮ እስከ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ድረስ ያለው አካባቢን ለአንድ ኳታራዊ ባለሃብት ለሆቴል መስሪያ እና ለቻይናዊ ባለሃብት ደግሞ ለገበያ ማእከል ግንባታ የሚውል ከ10 ሽህ ካሬ በላይ ይዞታ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን በሶስት ቀናት ውስጥ በአስቸኳይ እንዲለቁ ትእዛዝ ተሰጥቶ ቤታቸው በላያቸው ላይ ማፍረስ ተጀምሯል። ይህን ተከትሎ ከ20 እስከ 40 ሽህ የሚገመቱ የሶስት ቀበሌ ነዋሪዎች መጠለያ አልባ ሆነዋል። የንግድ ቤቶቻቸው እና መኖሪያ ቤቶቻቸውን የተቀሙ የከተማዋ ነዋሪዎች ከስድስት ወራት በኋላስ የት እንወድቃለን? የሚል ስጋት ላይ ወድቀዋል።
የኮንዶሚኒየም ቤት የተሰጣቸውም ለቤተሰቦቻቸው በቂ ያልሆነ፣ ተሰርቶ ያላለቁ ባዶ ቤት፣ መብራት ውሃ እና ውሃ የሌለው ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት ያልተዘረጋለት፣ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። በሃላፊነት ላይ የተሾሙት ባለስልጣናትም ችግሮቻቸውን ሊሰሙላቸው ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን ሰሚ አጥተው ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ተባረው እቃቸውን በርካሽ ሽጠው ለመልቀቅ መገደዳቸውን ማረፊያ አልባ ሆነዋል። የደረሰባቸው በደል ዜግነታቸውን እንዲጠራጠሩ እንዳረጋቸው በምሬት ተናግረዋል።
ቤታቸው በላያቸው ላይ እንዲፈርስ ተደርጎ እንዲፈናቀሉ ከተደረጉት ነዋሪዎች ውስጥ ባለፈው ዓመት በሊቢያ ልጆቻቸው የተገደሉባቸው ቤተሰቦችም ይገኙበታል። በመገናኛ ብዙሃን የሚነገረው መልካም አስተዳደር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የመናገር, የመጻፍ የመንቀሳቀስ መብት የሚባለው በተግባር የማይፈጸም ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እየተሳናቸው መምጣቱንም አክለው ገልጸዋል።
ነባር የቀበሌ ቤት፣ የኪራይ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የከተማ ነዋሪዎችን በግፍ በማስለቀቅ ለህወሃት ኢህአዴግ ካድሬዎች ቤቶችን ማከፋፈልም ተጀምርዋል። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙሰማ ነዋሪዎቹ በአፋጣኝ መኖሪያ ቤታቸው እንዲለቁ ከሚያስገድድዱ ባለስልጣናት ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።