መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደንቢያ ወረዳ ጎርጎራ አካባቢ በሚገኘው የቻይና ካምፕ ላይ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ሃይሎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ኩባንያው ሰራተኞችንና መኪኖችን ወደ ቆላ ድባ ካስወጣ በሁዋላ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው በመጓዝ አካባቢውን ማረጋጋቱን በመግለጽ፣ ኩባንያው ወደ ቦታው እንዲመለስ ቢያደርግም፣ ዛሬ አርብ በደረሰ ተጨማሪ የቦንብ ጥቃት ተሽከርካሪዎች እንደገና አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።
ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት ባለበት ሁኔታ ተጨማሪ ጥቃት መፈጸሙ የኩባንያውን ሰራተኞች አስደንግጧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቆላ ድባ የሚሊሺያ አዛዥ አቶ ይስማው ጌጡ እንዲሁም የሰራባ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ እንዳለውም መታሰራቸው ታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቆላ ድባ የቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎች ዛሬ አርብ ተቃውሞ አድርገው ውለዋል። የተቃውሞው መነሻ ትምህርት ቤቱ ቁጠባ ለመቆጠብ ያልቻሉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ አይገኙም በማለቱ ነው። ተማሪዎቹ “ ለሌባ ድርጅት አንቆጥብም” በማለት በግቢያቸው ተቃውሞ ሲያሰሙ ውለዋል።
በሌላ በኩል በባህርዳር ለሁለተኛ ቀን የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማዋ መግቢያና መውጨ ላይ ፍተሻ ሲያደርጉ ውለዋል። ትናንት የመካላከያ አባላት በወታደራዊ ተሽከርከሪዎች ተጭነው በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ከዋሉ በሁዋላ ዛሬ ወደ ፍተሻ ገብተዋል።