ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2009)
አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ የበለጸጉ ሃገራት ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትና ድርቅ ጋር በተያየዘ ሊሰጥ የነበረ የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዳይሰጥ ተቃወሙ።
ግሪን ክላይሜት ፈንድ (Green Climate Fund) የተሰኘና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚገኝ የአካባቢ ልማት ፕሮጄክት በደቡብ ኮሪያ ሰንግዶ ከተማ እያካሄደ ባለው ጉባዔ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በታሰበው የገንዘብ ድጋፍ ረቡዕ ምክክር መጀመሩን ክላይሜት ሆም የተሰኘ የአካባቢ የመገናኛ አውታር ዘግቧል።
ይሁንና የግሪን ክላይሜት ፈንድ የቦርድ አባላት ለኢትዮጵያ እንዲለቀቅ በታሰበው የገንዘብ ድጋፍ ላይ መከፋፈል ማሳይታቸው ታውቋል።
የአሜሪካ የካናዳ እንዲሁም በርካታ የበለጸጉ ሃገራት መንግስታት ተወካዮች የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ መሰጠት የለበትም የሚል ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸውን የዜና ወኪሉ በሪፖርቱ አመልክቷል።
በግሪን ክላይሜት ፈንድ የተካሄደ የባለሙያዎች አጥኚ ቡድን ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የታሰበው ድጋፍ ደካማና የፈጠራ ስራ እንዲዳብር ያስቀመጠው አቅጣጫ የለም ሲል ድምዳሜ ማቅረቡንም ለመረዳት ተችሏል።
ግሎባል ክላይሜት ፈንድ በበኩሉ የገንዘብ ድጋፍ የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የተሻለ የውሃ አቅርቦትና የግብርና ስልትን እንዲያገኙ የሚረዳ ነው ሲል በቀረፀው ፕሮጄክቱ ማስገንዘቡን የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከግማሽ በላይ ሴቶች የሆኑ ወደ 2.5 ሚሊዮን አካባቢ ሰዎች በፕሮጄክቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ቢቀመጥም የገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን፣ የቀረበው ሃሳብ ደካማ መሆኑንና ተረጂነትን የሚያበረታታ እንደሆነ አስታውቋል። በዚሁ ሃሳብ ዙሪያ መምከር የጀመሩት የድርጅቱ የቦርድ አባላት ሰፊ ክርክርን ካካሄዱ በኋላ አሜሪካ ካናዳ ኣንዲሁም የበለጸጉ ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንዳይሰጥ ተቃውሞን አቅርበዋል።
ይሁንና የታዳጊ ሃገራት ተወካዮች ባለሙያዎች የቀረበው ጥናት አድሎ የታየበት ነው ሲሉ ቅሬታን አሰምተዋል።
በግሪን ክላይሜት ፈንድ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቦርድ አባላት የሆኑት ቶሲ ምፓኑ ምፓኑ የኢትዮጵያ ተወካዮች ወደ ሃገራቸው ባዶ እጃቸውን እንዲመለሱ ከተደረገ ድርጊቱ ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል ሲሉ ከክላይሜት ሆም ገልጸዋል። በቅርቡ ፈንድ በተመሳሳይ ሁኔታ ለባንግላዴሽ ያቀረበው የገንዘብ ድጋፍ ተቃውሞ ቀርቦበት ሃገሪቱ ተጠቃሚ ሳትሆን መቅረቷም ታውቋል።
የቀረበን ተቃውሞ በተመለከተ የኢትዮጵያ ተወካዮች የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአካባቢ ጥበቃ ላይ ይዞታል የተባለው አዲስ ሃሳብ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑም ተመልክቷል።