ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2009)
በዋልድባ ገዳም አካባቢ በአማራና በትግራይ ሚሊሺያዎች መካከል ለሁለት ቀን የተካሄደው ግጭት በስፍራው አዲስ ውጥረት ማንገሱን አንድ አለም አቀፍ ተቋም ሃሙስ አስታውቋል።
ይኸው በመከላከያና ደህንነት ዙሪያ የሚሰራውና መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው ጄን የተሰኘ ተቋም ለሁለት ቀን በዘለቀው የሁለቱ ወገኖች ግጭት በትንሹ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። የአይን እማኞች በዋድባ እምበርታት ገዳም መጋቢት 27 2009 አም በሚከበረው የመድሃኒያለም ክብረበዓል ላይ ለመታደም ይጓዙ የነበሩ የአማራ ክልል ሚሊሺያዎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ በመጠየቃቸው ግጭት ሊቀሰቅስ መቻሉን ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
ተመሳሳይ ሪፖርትን ያቀረበው የደህንነት ተቋሙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሳምንቱ መጀመሪያ 39 መነኮሳት በቁጥጥር ስር አውለው እንደነበርም አመልክቷል።
መንግስት በዋልድባ ገዳም ዙሪያ ሊያካሄድ ያሰበው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ በገዳሙ ባሉ መነኮሳት በኩል ለአመታት ተቃውሞ እንዲቀጥል ማድረጉ ይታወሳል።
ሰሞኑን ገዳሙ ለልማት መነካት የለበትም በሚል መጠነ ሰፊ ዘመቻን ሊያካሄዱ የነበሩት አባ ገብረየሱስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
የዋልድባን እንታደግ ማህበር በበኩሉ የሃይልማኖት አባቱ በጸጥታ ሃይሎች በተያዙ ጊዜ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና ከቀናት በፊት ወደ ማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት ስለመወሰዳቸው መረጃ እንደደረሰው ለኢሳት መግለፁም አይዘነጋም።
በገዳሙ ዙሪያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም ዕልባት አለማግኘቱን ለኢሳት የገለፁት እማኖች ሰሞኑን ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ የበዓሉ አካባበሩ ባይስተጓጎልም ከበዓሉ ስነስርዓት በመመለስ ላይ የነበሩ ሰዎች መታገታቸው ታውቋል።