ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2009)
በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ በጎንደር ከተማ በሚገኘው የፍሎሪዳ አለም አቀፍ ሆቴል ላይ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ ተከትሎ የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሃሙስ አሳሰበ።
የከተማዋ ነዋሪዎች በሆቴሉ ላይ በደረሰው ጥቃት በትንሹ ሶስት ሰዎች መጎዳታቸውንና ድርጊቱ በከተማው አዲስ ውጥረት ማንገሱን ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል። መንግስት ሰለቦንቡ አደጋ እስካሁን ድረስ የገለጸው ነገር ባይኖርም የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለአደጋው ሃሙስ ባወጣው መግለጫው አረጋግጧል።
ሚኒስትሩ ለሃገሪቱ ዜጎች ባሰራቸው የጉዞ ማሳሰቢያ በጎንደር ከተማ ያሉ የብሪታኒያ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የክልሉ ባለስልጣናት የሚሰጧቸው ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በአለም አቀፉ ሆቴል ላይ የደረሰው ፍንዳታ የእጅ ቦንብ መሆኑን የገለጸው የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም አመልክቷል።
ከወራት በፊት በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች በሚገኙ ሆቴሎች ላይ ተመሳሳይ አደጋ ደርሶም እንደነበር ሚኒስቴሩ በማሳሰቢያ መልዕክቱ አውስቷል።
ባለፈው አመት ሃምሌ ወር በአማራ ክልል በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት ዜጎች አስቸኳይ ካልሆነ በስተቀር ወደ ፀገዴ፣ እንዲሁም ምዕራብና ታች አርማጭሆ የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች እንዳይጓዙ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።
ይኸው የጉዞ እገዳ አሁንም ድረስ ተግባራዊ ሆኖ መቀጠሉን የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎቹ ባሰራጨው የጉዞ ማሳሰቢያው አስፍሯል። በየአመቱ ወደ 20 ሺ አካባቢ የሚጠጉ ብሪታኒያውያን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት በጥቅምት ወር ተግባራዊ ያደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በርካታ የአስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የነበረውን የጉብኝት ፕሮግራም እንዲሰርዙት ሲዘግብ ቆይቷል።
የአሜሪካ መንግስት በዚሁ አዋጅ ምክንያት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ቢጓዙ መጉላላት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በማሳሰብ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክሩን ለግሷል።
የተለያዩ ሃገራት የወሰዱንት ተመሳሳይ ዕርምጃ ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ መጎዳቱን መንግስት አረጋግጧል።
ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ በሚገኘው የፍሎሪዳ አለም አቀፍ ሆቴል ላይ የደረሰው የእጅ ቦምብ ጥቃትም በቱሪስቶችና በነዋሪው ዘንድ አዲስ ስጋት ማሳደሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
በዚሁ ፍንዳታ በሆቴሉ መስኮቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ዕማኞች ከአደጋው በኋላ ቁጥራቸው ያልታወቀ ነዋሪዎች በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አክለው አስረድተዋል።