መጋቢት ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዚያው በደንቢያ የሚሊሺያ ሃላፊው ህዝቤን መሳሪያ አላስገፍፍም በማለት ራሱን አጥፍቷል።
ለኢሳት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት የአርሶአደሩን መሬት ያለበቂ ካሳ በመንጠቅ እንዲሁም በሰራተኞች ላይ በደል በማድረስ በሚታወቀው ጎርጎራ አካባቢ በሚገኘው የቻይና ካምፕ ላይ መጋቢት 25 እና 26 በተፈጸመው ጥቃት 3 ሰዎች መገደላቸውን እና በበርካታ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ፣ የመንገድ ስራ ድርጅቱ አካባቢውን ለቆ ወደ ቆላ ድባ ከተማ ገብቷል።
ጥቃቱን ተከትሎ የአካባቢው የኢህአዴግ አባላት የነበሩ ፣ሊቀመንበሩና ም/ል አስተዳዳዳሪው እንዲሁም የድርጅቱ ዘበኞች ታስረዋል። በርካታ የድርጅቱ ስራተኞችም ኩባንያውን ለቀው ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሄደዋል።
በአካባቢው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት፣ በቀበሌው ውስጥ ያለውን የጦር መሳሪያ ብዛት እስከ ነገ ጽፎ እንዲያመጣ ሲጠይቅ፣አቶ ሰንደቁ ይርዳው የተባሉ የአካባቢው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ፣ የወጣቶች አደራጅና የቀበሌ ሊቀመንበር “ህዝቤን መሳሪያውን አላስገፍምም፣ አላዋርደውም” በማለት በያዘው አብራራው ጠመንጃ ራሱን መግደሉን እና የቀብሩ ስነስርዓት ዛሬ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሎአል። በቀብር ስነስርዓቱ ላይ በሁለት ኦራል የመጡ ወታደሮች ህዝቡ መሳሪያውን እንዲያሰረክብ ሲያሰቃዩት ውለዋል።
ጣና በለስ ሰራቫ ፕሮጀክት፣ ለ6 ቀበሌዎች ታስቦ በ2005 ዓም ላይ የተጀመረ ቢሆንም፣ ድርጅቱ ለአርሶአደሮች በቂ የሆነ የመሬት ካሳ ሳይከፍል ማሳቸውን በማውደሙና ቤታቸውን በማፍረስ መጠለያ አልባ በማድረጉ በርካታ አርሶአደሮች በረሃብ እንዲሰቃዩ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። ከዚህም አልፎ በአካባቢው የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የድርጅቱን ካምፕ ወታደሮች መጠለያ አድርገው፣ የካሳ ክፍያ የሚጠይቁ አርሶአደሮችን ሲያሰቃዩበት ቆይተዋል።
በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ከፍተኛ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ
በሌላ በኩል በምእራብ ጎጃም ዞን በዳንግላ ወረዳ በህዝባዊ ተቃዉሞ ወቅት ቤት ለተቃጠለባቸው የወረዳና የከተማ አመራሮች ቤታቸዉን መልሶ ለመገንባት የዳንግላ ክተማ ነዋሪዎች መዋጮ እንዲያዋጡ እየተገደዱ ነው። የቀበሌ አመራሮች ቤት ለቤት በመዞር ህዝቡ ገንዘብ እንዲያዋጣ እያስገደዱት ነው፡፡ ነዋሪዎች ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ቀበሌዎች ሲሄዱ እንዲከፍሉ የሚጠየቁ ሲሆን፣ ለምን ብለው የጠየቁ ሰዎች አገልግሎት አያገኙም።