መጋቢት ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እንደ ግንባሩ መግለጫ በምስራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ በጥቂት ቀናት ውስጥ እየተዛመተ በመጣው የኮሌራ ተላላፊ በሽታ ምክንያት ከመቶ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተለይ የዶሎ፣ ቆራሄ፣ ኖጎቦ፣ ጃራር እና አፍዴር ወረዳዎች ክፉኛ ተጠቅተዋል።
ከኮሌራው ወረሽኝ በሽታው በተጨማሪ በቀጠናው እየተስፋፋ የመጣው መጠነ ሰፊ የድርቅ አደጋ በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ሰባአዊ ቀውስ እያስከተለ ቢሆንም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እስካሁን አፋጣኝ ምላሽ አልሰጠም ብሏል ኦብነግ:: የአካባቢው ባለስልጣናት የድርቁን ተጠቂዎች ምንዱባን ሕይወት ለመታደግ እርዳታ ከማቅረብ ይልቅ በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሕጻናትን እና አዛውንቶችን ምስል በማህበራዊ ድረገጾች በመለጠፍ ማሳየትን መርጠዋል።
ቁጥራቸው በይፋ በሪፖርት ያልተገለጹ አያሌ ዜጎችን ያለቁበትን የኮሌራ ወረሽኝ ሆን ተብሎ በገዥው መንግስት በተወሰነ የኦጋዴን አካባቢዎች የተከሰተ በማስመሰል እንዲሸፋፈን ተደርጓል ሲልም ኦብነግ ከሷል።
ኦብነግ በመግለጫው “የኦጋዴን አካባቢ ነዋሪዎች በተላላፊ በሽታዎች እና በድርቅ እንዲያልቁ ሆን ተብሎ አትኩሮት ባለመስጠት እንዲሞቱ እየተደረጉ ነው። አሳስቢነቱ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የርሃብ አደጋ ከእለት ወደ እለት አድማሱን በማስፋት በነዋሪዎቹ ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ፈጥሮባቸዋል። በገዥው ፓርቲ አቀነባባሪነት እንደዚህ ዓይነት የጅምላ እልቂቶች በህዝቡ ላይ ሲፈጸሙ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም”ብሏል
በዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ዋና ሚና ላላቸው የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ለአሜሪካ መንግስ፣ ለዓለምአቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ እንዲሁም ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች አፋጣኝ እርዳታ እንዲያቀርቡ ሲል የኦጋዴን ሕዝቦች ነጻነት ግንባር ኦብነግ ጠይቋል። በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በማውገዝና የሕዝቡን ሕይወት ለመታደግም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እገዛውን እንዲያደርግ ሲልም ግንባሩ ጥሪ አቅርቧል።