በኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ ንረት ወደ 8.7 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገለጸ

ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በማሻቀብ ላይ ያለን የምግብ ዋጋ ንረት ተከትሎ የመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበት ከሰባት በመቶ ወደ 8.5 በመቶ ከፍ ማለቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የወተት ተዋጽዖን ጨምሮ በስጋና በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መመዝገቡን የገለጸው ኤጀንሲው በተለይ የምግብ ዋጋ ባለፈው ወር ከነበረበት የ7.8 ወደ 9.6 በመቶ ሊያድግ መቻሉን መንግስታዊ ድርጅቱ በሪፖርቱ አመልክቷል።

በተለያዩ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው የምግብ ዋጋ ጭማሪው ከተያዘው አመት መግቢያ ጀምሮ ቅናሽን ሳያሳይ በመጨመር ላይ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።

በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋጋ ንረቱ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በአብዛኛው ገቢያቸውን በምግብ ወጪ ለማዋል መገደዳቸውንም አስታወቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በሃገሪቱ በአራት ክልሎች ተከስቶ ያለው አዲስ የድርቅ አደጋ ለምግብ እጥረትና ዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑን ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።

ድርጅቱ በሶማሌ ክልል ላሉ ተረጂዎች ገንዘብ በመስጠት የምግብ እጥረታቸውን እንዲቀርፉ ጥረት ቢያደርግም ሊሰጥ ያሰበው የገንዘብ መጠን ምግብ ለመግዛት የማይበቃ በመሆኑ ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ ገልጿል።

በክልሉ የሚካሄደው የእርዳታ አቅርቦት ከውጭ በሚገባ የምግብ ድጋፍ እንዲሆን መደረጉን ድርጅቱ አክሎ አመልክቷል።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በበኩሉ በመጋቢት ወር የተመዘገበው የምግብ ዋጋ ጭማሪ ካለፉት ጥቂት ወራት ጋር ሲነጻጻር በመጠን ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን በሪፖርቱ አስፍሯል።

በምግብ ነክ ላይ ከተመዘገበው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በተጨማሪ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ላይም በመጋቢት ወር የ1.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ሰባት በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በድረገፁ ካሰፈረው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከውጭ በሚገቡ ሸቀጣሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረትን እና እጥረትን በማስከተሉ ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋጽዖ ማድረጉን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሳቢያ የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገቡ ነጋዴዎች በፈለጉት መጠንና ወቅት ሸቀጣሸቀጦቹን ለተጠቃሚ ማቅረብ እንዳልቻሉ አስረደተዋል።

እነዚሁ አስመጪ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ ፈቃድን ለማግኘት ለወራት ወረፋን እንደሚጠብቁና በንግድ ስራቸው ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩን አክለው ገልጸዋል። የአለም ባንክ ኢትዮጵያ ያጋጠማት የውጭ ንግድ ማሽቆልቆልና ምንዛሪ እጥረት ለዋጋ ግሽበት ምክንያት ይሆናል ሲል በተደጋጋሚ ማሳሰቡ ይታወሳል።