መጋቢት ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በንቅናቄው ከፍተኛ አመራር በአቶ ኤፍሬም ማዴቦ የተመራው ይህ የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም እስካሁን በሜልበርን ፣በኒውዝላንድ ፣በኦክላንድ በክራይስት ቸርች ፣ በዊሊንግተን፣ በአውስትራሊያ በፐርዝ፣ በብሪዝበን፣ በሜልቦርን ፣ በኮሪያ ሴኡል እና ብጃፓን ቶኪዮ በከፍተኛ ስኬትና ድምቀት ተከናወኗል።
ከኤርትራ በርሃ በቀጥታ ወደ አውስትራልያ የመጡት የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ፕግራሞቹ በተዘጋጁባችወ አዳራሾች ሲገኙ ለስብሰባው የታደመው ኢትዮጵያዊ ከተቀመጠበት በመነሳት በእልልታና በጭብጨባ አድናቆትና ክብሩን ገልጾላቸዋል።
በተለይ የወልቃይት ማንነት ላይ ትኩረት አድርገው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኤፍሬም ወልቃይት መቼም ቢኾን በትግራይ ክልል ስር ሆኖ እንደማታውቅ የታሪክ ስዎችን እማኝነት በመጥቀስ አብራርተዋል።
በተለይ በዚህ ጉዳይ በቀ.ኃ.ሥ መንግስት የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩም የሰጡትን ምስክርነት ያደነቁት አቶ ኤፍሬም፤”የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ መመለስ ያለበት በመንግስት ወይም በየትኛውም አካል ሳይሆን በራሱ በወልቃይት ህዝብ ፍላጎት ብቻ ነው”ብለዋል።
በሜልቦርኑ ስብሰባ ከተሳታፊዎች ለአቶ ኤፍሬም “የወቅቱ የአግ7 እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ?፣ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር በህብረት የመስራቱ ነገር ምን ደረጃ ደርሷል? እና የአግ7 ሰራዊት ጥንካሬ ምን ያህል ነው?” የሚሉ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል።
አቶ ኤፍሬም ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ አግ7ም ሆነ የትኛው ተቃዋሚ ወገን በመንግስትነት ከተስየመው ወያኔ ጋር የሚያደርገውን ትግል ብቻውን ሊወጣው እንደማይችልና በህብረት መስራቱ የግድ መሆኑን በመጥቀስ “እኛም እንደ አግ7 ይህንን ዕውነታ ጠንቅቀን በማወቃችን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በትብብር የምንሰራበትን መንገድ ከመሻት ቦዝነን አናውቅም። ጥምረቱም የዚሁ ውጤት ነው” ብለዋል።
የቋጠሮ ድረ ገጸ አዝጋጅ ጋዜጠኛ ሳምሶን ከስፍራው ባጠናቀረው ሪፖርት ፦“በእለቱ የድጋፍ ማሰባሰብ ፕሮግራም በግለሰቦች ይሰጥ የነበረው የገንዘብ መጠን ብዙዎችን ያስደመመና አብዛኛው የሜልበርን ኢትዮጵያዊ ለአግ7 የትግል እንቅስቃሴ ከፍተኛ ክብርና አድናቆት እንዳለው ያረጋገጠ እንደነበር በስፍራው ተገኝተን ተመልክተናል”ብሏል።
ጋዜጠኛ ሳምሶም አክሎም “ይህ መሆኑ ደግሞ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በርሃ ለሚገኙት አርበኞች ከፍተኛ የሞራል እገዛ እንደሚያደርግ የሚያጠያይቅ አይደለም።” ሲል አስተያዬቱን ሰጥቷል።
ይህ ባቶ ኤፍሬም ማዴቦ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ቀናትም በአደላይድ ፣ በሲድኒና በሌሎች በርካታ የውስትራሊያ ከተሞች እንደሚቀጥል ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።