ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2009)
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሽብርተኛ ላይ እየተደረገ ያለውን ዘመቻ ለማጠናከር ከግብፅ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ሰኞ ይፋ አድርገዋል።
ከቀድሞው የግብፅ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ ከስልጣን መወገድ በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ White House የተጋበዙት ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ በበኩላቸው ፕሬዚደንት ትራምፕ በጸረ-ሽብርተኛ ላይ የያዙትን አቋም እንደሚያደንቁና ተባብረው እንደሚሰሩ ምክክር መካሄዱን ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ሁለቱ መሪዎች ለሰዓታት በዝግ ባካሄዱት ውይይት በአለም ዙሪያ በተለይ በአፍሪካ ፅንፈኝነትና ሽብርተኝነትን መዋጋት በሚቻልበት ዙሪያ ሰፊ የሃሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን የአሜሪካ ባለልስጣናት አስረድተዋል።
ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞቹ መግለጫን የሰጡት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ከግብጻውያን ጎን ትቆማለች ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ አልሲሲ “የአሜሪካ ታላቅ ወዳጅና አጋር ናቸው” ሲሉም የግብፅ ፕሬዚደንት አሞካሽተዋል።
አሜሪካ ለግብፅ የምታደርገውን ወታደራዊ እገዛም ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደምታሸጋግር የአሜሪካው ፕሬዚደንት ለተጋባጁ ፕሬዚደንት አልሲሲ አረጋግጠዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት የግብፅን ፕሬዚደንት ወደ White House መጋበዝ ሃገሪቱ በግብፅ ላይ የነበራትን አመለካከትና አቋም የቀየረ እንደሆነም የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ለሃገሪቱ የሚሰጠውን ድጋፍ በማቋረጥ በግብፅ ላይ ፊቱን አዙሮ እንደቆየም ተንታኞች አስተድተዋል።
ይሁንና አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር አዲስ የውጭ ፖሊሲን በመከተል ከግብፅ ጋር ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን ለመዋጋት ጠንክሮ ለመስራት መወሰኑ ተነግሯል።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የሃገራቸው መከላከያ ሚኒስቴር በሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አሸባብ ላይ የአየር ጥቃትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲወስድ ልዩ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይኸው የሶማሊያ ጉዳይ በሁለቱ መሪዎች ውይይት ወቅት ይነሳ አይነሳ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ፕሬዚደንት ትራምፕና አልሲሲ በአፍሪካ የጸጥታና የሽብርተኛ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ታውቋል።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በሶማሊያ ሲያካሄድ በቆየው ጸረ-ሽብርተኛ ዘመቻ ኢትዮጵያን በዋና አጋርነት መርጦ መቆየቱንም አይዘነጋም።
ለዚሁ ዘመቻ ሲባል አሜሪካ በአርባ ምንጭ ከተማ ወታደራዊ የጦር ጣቢያን በማቋቋም በአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ላይ በሰው አልባ አውሮፓላኖች የታገዘ ወታደራዊ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።
ይሁንና አሜሪካ ጣቢያውን ባለፈው አመት ጥር ወር የዘጋች ሲሆን፣ ጣቢያው ቀጣይ እንዲሆን አሳማኝ ነገር አለመኖሩን በወቅቱ መግለጿም የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ካሰማራቻቸው ከ4ሺ በላይ ወታደሮች በተጨማሪ ቁጥሩ ያልታወቀ የተናጠል ወታደሮች በሶማሊያ አሰማርታ መቆየቷ ይታወቃል።
ይሁንና ከወራት በፊት እነዚሁ ወታደሮች ከበርካታ ወታደራዊ ይዞታዎች ጠቅልለው የወጡ ሲሆን፣ ታጣቂ ሃይሉም ቦታዎቹን መቆጣጠሩ ይነገራል።
የመንግስት ባለስልጣናት ውሳኔው ለስልት የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን በመግለፅ ታጣቂ ሃይሉ ለኢትዮጵያ የጸጥታ ስጋት አይሆንም ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።