ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ አህዮች እንዲታረዱና ስጋና ቆዳቸው ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ መወሰኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እያነጋገረ ሲሆን፣ በአፍሪካዊቷ ቡርኪናፋሶም ያስከተለው ቁጣ በኢትዮጵያ ሊደገም እንደሚችል የፖለቲካ ተመልካቾች ይገልጻሉ። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ድርጊቱ ተቃውሞና ቁጣ ማስከተሉን ማስታወስ ተችሏል። መንግስት ከእንግዲህ ፈቃድ አልሰጥም ያለ ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት የሰጠውን ግን አልሰረዘም።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ የታሰበው የአህያ ስጋ ለሃገር ውስጥ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ቢሮ በመክፈት ቁጥጥር እንዲያደርግ አስታውቋል።
በቢሾፍቱ ከተማ የተቋቋመው ይኸው ኩባንያ ስጋውን ለቬይትናም የሚያቀርብ ሲሆን፣ የአህያ ቆዳን ደግሞ ወደ ቻይና ለመላክ እቅድ እንዳለው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
በ80 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት የተቋቋመው ይኸው የቻይና ኩባንያ ለውጭ ገበያ ያቀርባል የተባለውን አህዮች ከቢሾፍቱ ከተማ ዙሪያ ካሉ ገበሬዎች ለመግዛት ማሰቡ ተነግሯል።
በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ስራውን የሚጀምረው የቻይናው ሻንዲንግ ዶንግ ኩባንያ ከሁለት ሳምንት በፊት የሙከራ ጊዜን በጀመረ ወቅት 300 አህዮችን ለእርድ ማዋሉም ታውቋል።
በቢሾፍቱ ከተማ ከተቋቋመው የአህያ ቄራ በተጨማሪ በሌላ የቻይና ኩባንያ የተመሰረተ የአህያ ቄራ በአሰላ ከተማ መኖሩንም ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ ከአራት አመት በፊት ከተሰጣቸው ሁለቱ ኩባንያዎች ውጭ ድርጊቱ ከሃገሪቱ ህዝብ ባህል እና እሴት ጋር የሚሄድ ባለመሆኑን ከዚህ በኋላ ለተመሳሳይ የአህያ ቄራ ፈቃድ አይሰጥም ሲል ምላልሽን ሰጥቷል።
ለቻይና ኩባንያዎቹ የመጀመሪያ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ መንግስት ፈቃድ እንዳልሰጠ መመሪያን አውጥቷል።
ይሁንና ድርጊቱ ከሃገሪቱ ህዝብ ባህልና እሴት ጋር የሚጻረር መሆኑን ከታወቀ የቀደመው ፈቃድ ለምን አይሰረዝም ለሚለው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሰጠው ማብራሪያ የለም።
የቻይናው ኩባንያ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ደበሌ ለማ በበኩላቸው በቢሾፍቱ ከተማ የተቋቋመው የአህያ ቄራ በየዕለቱ እርድ ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 አም በኢትዮጵያ በተካሄደ የእንስሳት ቆጠራ 7.4 ሚሊዮን አህያ በሃገሪቱ መኖሩ ተመልክቷል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አህያን ለውጭ ምርት እንዲቀርብ መወሰኑ ቁጥሩን ሊቀንስ እንደሚችል ተሰግቷል።
ባለፈው አመት አፍሪካዊቷ ቡርኪናፋሶ የአህያ ስጋንና ቆዳን በተመሳሳይ መንገድ ለኤዥያ ገበያ ለማቅረብ ብትወሰንም ዕርምጃው ተቃውሞን አስከትሎ የሃገሪቱ መንግስት ንግዱ እንዲቀር ማድረጉን CNN በወቅቱ መዘገቡን ለመረዳት ተችሏል።
በዚሁ ንግድ የተቆጡ የቡርኪናፋሶ ዜጎችም ከመዲናይቱ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው የባሎሌ ከተማ በተቋቋመ የአህያ ቄራ (እርድ) ድርጅት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያው አቅርቧል።
ቻይና የአህያ ቆዳን የተለያዩ መድሃኒቶችን ለማምረት የምትጠቀመው ሲሆን በሃገሪቱ ያሉ አህዮችን ለዚሁ ተግባር ማዋል በመጀመሯ የአህያ ቁጥር መቀነስ አጋጥሟት ፊቷን ወደ አፍሪካ ማዞሯን ከተለያዩ ጹሁፎች የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በኬንያ፣ ናይጀሪያና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም የአህያ ዕርድ በተለያዩ ጊዜያት ተቃውሞን መቀስቀሱ ታውቋል።