ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ጋዜጠኞቹ ማክሰኛ እለት በዋለው ችሎት እንደገለጡት ፣ ወደ ኦጋዴን ክልል የገቡት የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅትን ለመርዳት ሳይሆን በአካባቢው በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማራው ሉንዲን ኦይል የተባለውን የስዊዲሽ የነዳጅ ኩባንያ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሰሰውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት አባላት በዘበኝነት መቅጠሩን ለማረጋገጥ ነው።
ጋዜጠኛ ማርቲን ሺቢዬና ጆሀን ፔርሰን እንዳሉት ከኦብነግ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የጋዜጠኝነት ስነምግባርን በተከተለ መልኩ የተከናወነ ነው። ጋዜጠኞቹ ወታደራዊ ስልጠና አግኝተዋል በሚል አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስም ውድቅ አድረገውታል።
አቃቢ ህግ ያቀረበውና ማርቲን ሺቢዬ የጦር መሳሪያ ይዞ የሚታየው ፎቶ ግራፍ የተቀረጸው በአንድ ሆቴል ውስጥ ከአንድ የአልሸባብ ወታደርን ቃለ ምልልስ እያደረገ በነበረበት ጊዜ መሆኑን ፣ ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል።
የጋዜጠኞቹ ጠበቆች እንደሚሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች ከዚህ ቀደም አስቸጋሪ በሆኑ የጦርነት ቦታዎች ሳይቀር በመጓዝ ዘገባዎች ያቀረቡ ናቸው። ከ800 በላይ በአለም ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ለሁለቱ ጋዜጠኞች ምስክር ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ተናግረዋል።
የመለስ መንግስት ሳያውቅ በወሰደው እርምጃ የኦጋዴን ችግር የአለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት እንዲያገኝ እንደሚያደርገው የፖለቲካ አዋቂዎች ይናገራሉ።