መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እምነት ያጣንበት ሚኒስትር ዳግም እየተሾመ ነው ያሉት አቶ አባይ፤ የመንግስት አሠራር ካልተቀየረ ይች ሀገር በእሳት ትቃጠላለች ሲሊ አስጠንቅቀዋል።
ኢሳት በደረሰው የድምጽ መረጃ ላይ በፓርላማው የተለመደ የደቦና የጥድፊያ አሰራር ትችት የሰነዘሩት አቶ አባይ፤ ሹመትና በጀት ያለብስለትና ያለ እምነት በጥድፊያና በዘመቻ እየጸደቀ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን ጠቁመዋል።
ቋሚ ኮሚቲው ከአስፈጻሚው የመጣውን ማጽደቅ ሥራው ቢኾንም ኮሚቴው ብቃት ኖሮት ወይም ገብቶት ነው ወይ የሚያጸድቀው?”በማለት የጠየቁት አቶ አባይ ፣በተለይ ሹመትና በጀት እዚህ ሀገር ዝም ብሎ ነው የሚጸድቀው ብለዋል።
“አሜሪካም አብላጫ ውንበር ያለው ገዥ ፓርቲ ያቀረበው ህግና በጀት ነው የሚጸድቀው።ሆኖም እነሱ እንደኛ በሰዓታት አይደለም የሚያጸድቁት።አገላብጠው በደንብ ፈትሸው ነው እሚያጸድቁት” ያሉት አቶ አባይ፤ “የራሳቸው ፓርቲ ያስመረጠው ፕሬዚዳንት ያቀረበውን ጭምር በደንብ አገላብጠው አይተው እንጂ የሚያጸድቁት እንደኛ ዝም ብለው አይፈርሙም”ብለዋል።
አክለውም እኛም ጋር ይህ እንዲደረግ ድፍረቱ ካለ መጀመሪያ መስተካከል ያለበት ኢህአዴግ ከኢህአዴግም ካቢኔውና ሥራ አስፈጻሚው ነው ብለዋል። ይሁንና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ጸረ ዲሞክራሲ የተጠናወተውና ጸረ ዲሞክራሲ የገነገነበት ነው ያሉት የህወሃቱ መስራች፤ “ ይህ የኔ አስተያዪት ሳይሆን በጥቅል ተሀድሶው የደረስንበት ድምዳሜ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“አመራሩ እንኳን ያቀረብከውን ሹመትና በጀት አልተቀበልንህም ሲባል ጠንከር ያለ ጥያቄ ሲቀርብለት የሚያኮርፍ፣ የሚያንገራግርና አካኪ ዘራፍ የሚል ነው ”በማለትም የሥራ አስፈጻሚውን አምባገነንነት በግልጽ ነቅፈዋል።
“በጥልቅ ተሀድሶው ራሳችንን በህግና በዲሞክራሲያዊ ተቋማት አገዛዝ ካላስገዛን ጸረ ህዝብ ፓርቲ በመሆን ወደ ጸረ ህዝብ መንግስት እንቀየራለን የሚል መደምደሚያ ላይ ነው የደረስነው።” ያሉት አቶ አባይ ጸሀዬ፤ “እንኳን በኛ የኪራይ ሰብሳቢነት በሞላበት በሰለጠኑት ሀገራትም አስፈጻሚው በህግና በተቋማት ካልተያዘ ይፈነጫል፣ይባልጋል።እልም ያለ አምባገነን ይሖናል።”ብለዋል።
አያይዘውም “በመሆኑም የሚያጠፋ አካል ይመከር፣ ይስተካከል፤ ሆኖም የማይመከርና የማይስተካከል ከሆነ የሚወገድበትና ከዚያው ፓርቲ ሌላ ግለሰብ የሚተካበት አሰራር የሚከተል ምክር ቤት ሊሆን ይገባል”ሲሉ ሀሳብ አቅርበዋል።
አቶ አባይ በመቀጠልም፦”ይህች ሀገር እንዳትፈርስ፣ወደ ትርምስ እንዳትገባ ከተፈለገ መፍትሔው እሱ ብቻ ነው። አለበለዚያ ይች ሀገር በእሳት ትቀጣጠላለች።ይህን ኢህአዴግ ያውቃል።ህዝብም ያውቃል”” በሁለትና በሶስት ወር ውስጥ ምን አይነት እሳት መቀጣጠል ጀምሮ እንደነበር ዐይተነዋል”ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“እናውቀዋለን እኮ። በየአምስት ወሩና ስድስት ወሩ የሚቀደድ በርካታ ህግኮ ነው እዚህ አገር ያለው” ያሉት አቶ አባይ፤ “ ሥራ አስፈጻሚው ወይም ካቢኔው አንድን አዋጅ ላከ ማለት ያለቀለት መጽሀፍ ቅዱስ ወይም ቁርአን ማለት አይደለም። መቀየር ካለበት ሊቀየር ይገባል ”ብለዋል።
በዚሁ ኢሳት እጅ ውስጥ በገባው የድምጽ መረጃ “ሦስቴና አራቴ ያደረቀንና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ አቤቱታ ያቀረብንበት ሚኒስትርና የቢሮ ኃላፊ እንደገና ለምንድነው በሹመት የሚቀጥለው?”በማለት ሲጠይቁ የሚደመጡት አቶ አባይ “እምነት አላሳደርንበትም ያልነው አካል ይወገድ፤ አለበለዚያ በሚዲያ እናውጀዋለን” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።