የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ የጊዜ አዋጁን ማራዘሙ ሕዝባዊ ቁጣውን አያቆመውም ሲል የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታወቀ

መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት ማራዘሙን ለዓለምአቀፉ ማህበረስብ ማስታወቁ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ሊያስቆመው አይችልም ሲል የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ መግለጫ አወጣ። ሚሊዮኖችን ከነባር ይዞታ ያፈነቀለውን የመሬት ቅርምት በመቃወም እና በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በማውገዝ በሰላማዊ መንገድ ገዥው መንግስትን ሲቃወሙ የነበሩትን የአማራ እና ኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ”ጸረ ልማት ሃይሎች”በማለት ሰብዓዊ መብታቸውን በመጣስ ግድያ፣ የጅምላ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ተፈጽሞባቸዋል። ታላላቆቹ የአገሪቱ ብሄረሰቦች የኦሮሞ እና አማራ ተወላጅ ሰላማዊ ወጣቶችን በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ እንዲመሰረትባቸውም ተደርጓል። ገዥው ህወሃት ኢህአዴግ ፓርቲ በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በየቀኑ ግራአጋቢ የሃሰት መረጃዎችን በመንዛት አገሪቱ ወደ ቀድሞ ሰላሟ ተመልሳለች ቢልም ሁኔታዎቹ ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው። ሰላምና መረጋጋት አላት ተብሎ ሲዘገብ የነበረ ቢሆንም ሕጋዊ የግድያ አዋጅ የሚፈቅደውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመከላከያ ሚንስትር ሲራጅ ፈጌሳ አማካኝነት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ EBC ለቀጣይ አራት ወራት እንዲራዘም መደረጉ ታውጇል። የአስቸኳይ አዋጁን መራዘም ሕዝቡ መጠየቁንም ሚንስትሩ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል። አንባገነኑ የኢትዮጵያ መንግስት በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሞ እና ሶማሌ ብሔር ተወላጆች መሃከል ሆን ተብሎ ግጭቶችን በመፍጠር ሰላማዊ ዜጎች እንዲገደሉ እያደረገ ነው። በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ መከላከያ ሰራዊት ከልዩ ጦር ጋር በጋራ በመሆን የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ እልቂት እየተፈጸመ ነው። በሰሜን ኢትዮጵያም በተመሳሳይ በጎንደር እና አካባቢው የጅምላ ግድያዎች እየተፈጸሙ መሆኑንም የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታውቆ በገዥው ፓርቲ በሚታዘዘው አጋዚ ጦር በግፍ የተገደሉ የስም ዝርዝርም አውጥቷል። በማአከላዊ፣ በአዳማ ፖሊስ ማሰልጠኛ ማእከል አዲስ የሰቆቃ ቶርቸር እስር ቤቶች ውስጥ በሽዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ሰቆቃ እየተፈጸመ መሆኑንም የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ በሪፖርቱ ገልጾ አንባገነኑ መንግስት አስቸኳይ አዋጁን ተገን በማድረግ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን የመብት ጥሰት እንዲያቆም ሲል ሊጉ ጥሪውን አቅርቧል።