መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአዲስ አበባ 48 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ወይም ደብረዘይት የተገነባው የአህያ ማረጃ መጠናቀቁንና ሥራ መጀመሩን ተከትሎ ኢትዮጵያ የአህያ ሥጋ ለውጪ ገበያ ማቅረብ መጀመሯን ሳምንታዊው አዲስ ፎርቹን ዘግቧል።
እንደ መገናኛ ብዙሀን ሪፖርት ሻንዶንግ ዶንግ የተሰኘው የአህዮች ማረጃ ቄራ ግንባታ 80 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
ኩባንያው የአህያውን ሥጋ የሚልከው ወደ ቬትናም ሲሆን፣ ቆዳውን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለመድሀኒትነት ወደሚፈለገው ቻይና ነው። ፋብሪካው ከስድስ ወር በፊት በቢሾፍቱ በተቃዋሚዎች ጥቃት ደርሶበት ነበር።
ሌላ ተጨማሪ የአህያ ማረጃም በአርሲ-አሰላ ውስጥ በቻይናውያን እየተገነባ መሆኑን የዜና ምንጩ ጨምሮ ዘግቧል። በተለይ የመድሀኒትነቱ ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ቻይና የአህያ ቆዳ ፍላጎቷን ለማሟላት ፊቷን ወደ አፍሪቃ አዙራለች።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከኒጀር 80 ሺህ አህዮች ወደ ቻይና ኤክስፖርት ተደርገዋል። በዚህም ምክንያት በኒጀር 34 ዶላር የነበረው የአንድ አህያ ዋጋ 147 ዶላር መድረሱ ተዘግቧል።የቻይናውያንን ፍላጎት ለማሟላት በጎረቤት ኬንያ ናይቫሻ ውስጥ የተገነባው የአህያ ማረጃ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።
ይህ አህያ የማረዱ ተግባር በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሀይማኖትና ባህል ዘንድ እንደ ነውር የሚቆጠር በመኾኑ ዜናው ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።