ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2009)
የብሪታኒያ መንግስት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰብዓዊ መብት ረገጣ ለሚታወቁት ሃገራት ለስለላ የሚረዱ ቁሳቁሶችንና የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አንድ አለም አቀፍ ተቋም አስታወቀ።
ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሳውዲ አረቢያ፣ ባህሬንና፣ የቤንዙዌላ መንግስታት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን በመገናኛና በማህበረሰብ መብት መከበር ዙሪያ የሚሰራው ግሎባል ቮይስ የተለያዩ አካላትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
መቀመጫውን በኔዘርላንድ አምስተርዳም ከተማ ያደረገው ይኸው ተቋም፣ ብሪታኒያ ከአሜሪካ በመቀጠል በአለም የጦር መሳሪያን በመሸጥና በማቅርብ ሁለተኛ ሃገር መሆኗን አመልክቷል።
የብሪታኒያ መንግስት የረቀቁ ለስለላ የሚረዱ ቁሳቁሶችንና የጦር መሳሪያዎችን ከምታቀርብላቸው ሃገራት መካከል በሰብዓዊ መብት ረገጣቸው የሚታወቁ ሃገራት መካተታቸውን ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
ሳውዲ አረቢያ በየመን እያካሄደች ላለው ጦርነት ከብሪታኒያ የክላስተር ቦንብን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ስትቀበል መሰንበቷን ግሎባል ቦይስ የጦር መሳሪያ ንግድ እንዲቆም ዘመቻን እያካሄዱ ያሉ አካላትን ዋቢ በማድረግ አቅርቧል።
ሃገሪቱ በሚስጥር ይህንኑ ቁሳቁስ ከምታቀርብላቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የፓርላማ አባላት ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ስልጠናን ታደርጋለች በማለት ተቃውሞ ሲያቀርቡ ቆይቷል።
ብሪታኒያ በአለም አቀፍ ደረጃ ለስለላ የሚረዱ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ግንባር ቀደም ሃገር እንደሆነች ያመለከተው የማህበረሰብ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፣ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 አም የተባበሩት አረብ ኤሜሬት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን ለመበተን የሚረዱ የ6.1 ሚሊዮን ዶላር ቁሳቁስ መረከቧን አክሎ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመሰናበት በሂደት ላይ የምትገኘው ብሪታኒያ፣ ከህብረቱ መሰናበቷ በጦር መሳሪያ ንግዷ እንድትገፋበት የሚያደርግ ለመሆኑ የፓርላማ አባል የሆኑት ዴቪድ ጆንስ አስታውቀዋል።
“Stop the Arms Fair” የሚል መጠሪያ ያለው እና የጦር መሳሪያ ንግድ እንዲቆም ዘመቻን የሚያካሄድ ተቋም የፊታችን መስከረም ወር በብሪታኒያ ሊካሄድ የታቀደ አለም አቀፍ የመከላከያና የደህንነት መድረክ እንዲቀር ቅስቀሳ መጀመሩን ገልጿል።
ከ30ሺ በላይ ተሳታፊዎች ከተለያዩ ሃገራት የሚሰባሰቡበት ይኸው መድረክ የመከላከያ ሚኒስትሮች እንዲሁም የጦር መሳሪያ ንግድ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ድርጅቱ አስታውቋል።
የብሪታኒያ መንግስት እያደገ ያለው የጦር መሳሪያ ንግድ እንዲያበቃ ዘመቻን እያካሄዱ ያሉ የሃገሪቱ ድርጅቶች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ እንደነበርም ታውቋል።
ይሁንና ሃገሪቱ ያየዘችው አቋም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተለያየ አቋም በማንጸባረቁ ምክንያት ዕልባት ሳያገኝ መቆየቱን ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያም ሆነች በሪፖርቱ የተጠቀሱ ሃገራት መረጃውን በተመለከተ የሰጡት ምላሽም ሆነ ማስተባበያ የለም።