ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2009)
የቀድሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚደንት አቶ ማሙሸት አማረ ከወንድማቸው ጋር በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ታወቀ።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት አቶ ማሙሸት ከወራት በፊት ከደረሰባቸው የጤና እክል ተከትሎ ጸበል በመከታተል ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል።
የአቶ ማሙሸት አማረ ወንድም የሆኑት አቶ ግዛቸው አማረ፣ ለወንድማቸው ስንቅ ለማቀበል በሄዱ ጊዜ በአንድ ላይ በኮማንድ ፖስት አባላት ታፍነው መወሰደዳቸውን ለመረዳት ተችሏል።
የቀድሞው የመኢአድ ፕሬዚደንት ከዚህ በፊት በነበራቸው የፖለቲካ አመራርነት ከፕሮፌሰር አስራት ጋር ለሰባት አመታት ታስረው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
አቶ ማሙሸት አማረ ከረጅም የእስር ጊዜ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ፖለቲካ ስራቸው ቢመለሱም ከ1997 ብሄራዊ ምርጫ በኋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሁለት ጊዜ ለእስር ተዳርገው እንደነበርም የቅርብ ቤተሰብ አባሎቻቸው ለኢሳት አስረድተዋል።
አቶ ማሙሸት አማረ ከነወንድማቸው ጋር በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው ለቤተሰብ ቢገልጽም፣ የቀድሞ የመኢአድ ፕሬዚደንት ከወንድማቸው ያሉበት የእስር ቦታ እንዳማይታወቅ የኢሳት ምንጮች ለዜና ክፍላችን ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲሁም በርካታ የፓርቲው አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራቶች እንዲራዘም ሃሙስ መወሰኑ ይታወሳል።