ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 11 በተለምዶ ፈለገ-ዮርዳኖች ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ አማራጭና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ለረጅም ጊዜ የኖሩበትን የመኖሪያ አካባቢ ማፍረስ መጀመሩን አስታወቁ።
ሜክሲኮ ተብሎ ከሚጠራ አደባባይ ወደ ቄራ በሚወስደው ዋና መንገድ ዙሪያ የሚገኙ እነዚሁ ነዋሪዎች አካባቢው ለልማት ይፈለጋል ተብለው በሃይል እንዲለቁ በመደረግ ላይ መሆኑን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለልማት ይፋለጋሉ ተብሎ ከመኖሪያ ቀያቸው የሚያፈናቅላቸው ሰዎች በመበራከታቸው በመዲናይቱ አዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የወረዳ 11 ሃላፊዎች ለነዋሪዎቹ የመጠለያ ቦታዎች እየተዘጋጀ መሆኑን ቢያስታውቁም ቅሬታ አቅራቢዎቹ የተባለው መጠለያ ሳይዘጋጅላቸው ቤታቸው እየፈረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቅርቡ በከተማዋ አደጋ ደርሶበት በነበረው በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችም ስፍራውን እንዲለቁ ቢነገራቸውም የከተማው አስተዳደር አማራጭ እና ምትክ ቦታ እንዳላቀረበላቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማውን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የያዘው እቅድ ሊሳካ ባለመቻሉ ከባለሃብቶች እየቀረበለት ያለን የመሬት ጥያቄ ለመመለስ ፊቱን በከተማዋ ማድረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
አስተዳደሩ በተያዘው በጀት አመት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለልማት ለማንሳት እቅድ እንዳለው ሲገልፅ ቆይቷል።
ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች ለመገንባት ቃል የገባው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በታሰበው መጠን ተግባራዊ ባለመደረጉ ተነሺ ነዋሪዎች የሚገቡበትን ቤት ማጣታቸው ታውቋል።
ችግሩን ለመቅረፍ አስተዳደሩ ተነሺዎች የግል መኖሪያ ቤት በጊዜያዊነት እንደተከራዩ ገንዘብ ለመስጠት ቢሞከርም ነዋሪዎቹ ገንዘቡ በግል ለመከራየት በቂ አለመሆኑን እየገለፁ ይገኛል።
በቂርቆስ፣ በቦሌ፣ ቡልቡላ፣ በላፍቶ ክፍለ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች እንደሚፈርሱም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።