በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰበት የሲቪል ሰርቪስ የምዘና ሂደት መከነ

መጋቢት ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የደኢህዴግ ከፍተኛ ካድሬ በሆኑት አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ለመተግበር እየሞከረ ያለው የመሠረታዊ የሥራ ሒደት (BPR) እና የውጤት ተኮር ሥርዓት (Balanced Score Card/BSC) ምዘና መምከኑን ምንጮች ገልጹ። የምዘና ዕቅዱ በሰራተኞች ተቀባይነት አጥቶ ቢከሽፍም፣ የኢህአዴግ አገዛዝ ግን ዕቅዱን ለማስፈጸም በሚል ዛሬም ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሰ ነው።
የሚኒስቴሩ ምንጮች ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት ቢፒአር እና ቢኤስ ሲ ሳይንሳዊና በበርካታ ሐገራት የሚሰራባቸው የሥራ ምዘና መሳሪያዎች ቢሆኑም፣ በኢትዮጵያ ግን ከፖለቲካ ጋር በመቀየጡ የመንግሥት ሰራተኞች አሠራሩን ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር መንፈጋቸው ለውድቀቱ አንድ መንስኤ ነው ፡፡
ሥርዓቱ በተለይ የመንግሥት ሠራተኛውን ለመቆጣጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ ሠራተኞች በአንድ ለአምስት ቡድን እንዲደራጁ በማድረግ ሠራተኛው እርስበርስ እንዲጠባበቅና እንዳይተማመን ማድረግ ቢችልም፣ አሠራሩ በሠራተኛው ያልተቋረጠ ትግልና ተቃውሞ በአብዛኛው የመንግስት መ/ቤቶች ሊከሽፍ ችሏል፡፡ አንድ ለአምስት አደረጃጀቱ በቀጠለባቸው በርካታ መ/ቤቶችም ቢሆን ከፍተኛ ባለሙያዎች ሥራቸውን እንዲለቅቁ ምክንያትም በመሆኑ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የባሰውኑ እንዲዳከም አድርጎታል።
የለውጥ መሳሪያዎቹ የፖለቲካ አቋም መፈተሻ ተደርገው ባይቀረጹ ኖሮ አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ ሰዎች በሥራ አፈጻጸማቸውና ብቃታቸው እየተመዘኑ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት ለመዘርጋት የሚረዳ እንደነበር የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ይናገራሉ።
ከ15 ኣመታት በፊት በአቶ ተፈራ ዋልዋ ይመራ የነበረው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር መ/ቤት የጀመራቸው የሲቪል ሰርቪስ የለውጥ ሥራዎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና ጊዜ ፈጅቶ ያለውጤት ባክኖ ከቀረ በሁዋላ ፣ ሚኒስቴሩ ልዩ ትኩረት ያሻዋል በሚል በከፍተኛ ካድሬዎች ማለትም በአቶ ኩማ ደመቅሳ፣ ጁነዲን ሳዶ፣ አስቴር ማሞና ሙክታር ከድር በተለያዩ ጊዜያት እንዲመሩት ቢደረግም የሚታይና የሚዳሰስ ውጤት ሊያስመዘግብ አልቻለም፡፡
የሚኒስቴሩ ምንጮች እንደሚናገሩት ለዚህ ዋና መንስኤው ኢህአዴግ የሲቪል ሰርቪስ የለውጥ መሣሪያዎቹን ተገን በማድረግ የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካትና በሠራተኛው ለማስረጽ መንቀሳቀሱ ነው፡፡
ኢህአዴግ፤ የለውጥ መሣሪያዎቹ ተግባራዊ መሆን ባለመቻላቸውና ግራ በመጋባቱም አንድ ጊዜ «የለውጥ ሠራዊት»፣ ሌላ ጊዜ« የሕዝብ ክንፍ»፣ ከዚያም «የመንግሥት ክንፍ »፣ እንዲሁም ዜጎች ቃል ኪዳን የሚገቡበት« የዜጎች ቻርተር» እያለ ሠራተኛውንና ህዝቡን ግራ ማጋባቱን ቀጥሎበታል ሲሉ ምንጮች ይገልጻሉ።
አገዛዙ ፖለቲካዊ ጫናውን በማንሳት ሠራተኞች በፈቃዳቸውና አምነውበት እንዲሳተፉ እንዲሁም በባለቤትነት ስሜት እንዲፈጽሙት ዕድል ካልተሰጠ በስተቀር፣ ወደፊትም ቢሆን እቅዱ የአገሪቱን አነስተኛ ሐብት ከማባከን ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በበርካታ የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሒደት እጅግ ተዳክሞና በሙስናና ብልሹ አሠራር ተተብትቦ ይገኛል። ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ “ጥልቅ ተሃድሶ” በሚል ግምገማ ቢደርግም ችግሩ እየባሰበት እንጅ እየቀነሰ አልሄደም።