አንድ የአሜሪካ የፓርላማ አባል ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው እርዳታ እንዲቋረጥ ጠየቁ

መጋቢት ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኮሎራዶ 6th ዲስትሪክት ተወካይ የሆኑት ማይክ ኮፍማን ለአገራቸው ምክር ቤት የውጭ እርዳታ አስተባባሪ ክፍል በጻፉት ደብዳቤ የኢህአዴግ መንግስት የሚፈጽመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እስኪቆም ድረስ በመጪው አመት ሊሰጥ የታሰበው የእርዳታ ገንዘብ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል።
“ዛሬ ይህንን ደብዳቤ እንድጽፍ ያደረገኝ እኔን የመረጡኝ አብዛኛዎቹ ኢትዮ-አሜሪካዊያንን ባቀረቡልኝ ጥያቄ መሰረት ነው። “ ያሉት የፓርላማ አባሉ፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚፈጽሟቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር እንዳስረዱዋቸው ገልጸዋል።
“ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል፣ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ይገላል፣ ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎች፣ አክቲቪስቶች እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጅምላ ያስራል። የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ነጻነታቸውን በማፈን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ጋዜጠኞች እንዳይደራጁ “ ይደረጋል ሲሉ ባለስልጣኑ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
“ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገራት የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ የአሜሪካ መንግስት እርዳታ ያደርጋል። መንግስታችን ይህን እርዳታ ከመስጠቱ አስቀድሞ የመንግስታቱን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዳግም ሊያጤነው ይገባል ብዬ አምናለሁ።” የሚሉት ማይክ ኮፍማን፣ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን በማጥበብ የራሱን ዜጎች ሰብዓዊ መብት በመጣስ በጭካኔ በመግደል ለሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ እና ድጎማ ልናደርግለት አይገባም ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።
የአሜሪካ መንግስት እንደፈረንጆች አቆጣጠር ለምጣኔ ሃብት እድገት፣ ለሰብዓዊ አገልግሎት፣ ለትምህርት፣ ለማህበራዊ አገልግሎት፣ እና ለጤና የሚውል በሚል ለኢትዮጵያ መንግስት የ514 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መመደቡ፣ የተቀደሰ ተግባር ቢሆንም፣ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ላይ ያጠኑ የተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡትን እርዳታዎች ለችግረኛው የአገሪቱ ሕዝብ በቀጥታ አይደርሰውም የሚሉት ኮፍማን፣ለኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ መስጠት ማለት ለሚፈጽማቸው የሰብዓዊመብት ጥሰቶች እውቅና እንደመስጠት ይቆጠራል ብለዋል።
የአሜሪካ መንግስት እኤአ በ2018 ለኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ እንዳይሰጥና እርዳታው በሰብአዊ መብት አያያዞች ላይ ተንተርሶ መለቀቅ እንዳለበት በደብዳቤያቸው ገልጸዋል። ማይክ ኮፍማን ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ደብዳቤ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጽፈው ነበር።