በድንበር አካባቢ ያለው ጸጥታ አለመረጋጋቱን ሚኒስትሩ አስታወቁ

መጋቢት ፳፩ (ሃያ አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሚቀጥሉት አራት ወራት እንዲራዘም ለተወካዮች ምክርቤት ጥያቄ አቅርበው የተፈቀዳላቸው የወታደራዊ እዙ ( ኮማንድ ፖስት) ዋና ጸሃፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገው ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ጸረ ሰላም ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ በአማራ ክልል በትግራይና አማራ ፣ በኦሮምያ እና በሶማሊ እንዲሁም በቤንሻንጉልና በአማራ ድንበሮች አካባቢ ጦርነቶች እየተደረጉ መሆኑን ኢሳትን ጨምሮ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ሲያቀርቡት የነበረውን ዘገባ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ ተቃውሞውን የሚመሩትን መሪዎች በአብዛኛው መያዝ ቢቻልም፣ አሁንም ያልተያዙ እንዳሉ እንዲሁም አልፎ አልፎ ጽሁፎች እንደሚበተኑ ተናግረዋል። አዋጁ እንዲራዘም መደረጉ በእነዚህ የድንበር አካባቢዎች የሚደረጉት ትግሎች ከባድ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ታጋይ ከኢትዮጵያ ገልጸዋል። የአዋጁ መራዘም የሚያሳየው የእኛ ትግል ፈተና ውስጥ እየከተታቸው መሆኑን ነው የሚሉት ታጋዩ፣ በሚቀጥሉት አራት ወራትም ትግሉ እስካሁን ከተካሄደው በበለጠ መጠን ይካሄዳል ብለዋል።
አቶ ሲራጅ አሁን የተገኘው ሰላም ሊቀለበስ ይችላል በማለት ስጋታቸው የገለጹ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም ይህንኑ አስተያየቱን አጠናክሯል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ላይ የደረሰው ኪሳራ በሪፖርቱ አልተገለጸም። ይሁን እንጅ ኢሳት ሰሞኑን ባቀረበው ዘገባ አዋጁ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል። አዋጁ የሚራዘም ከሆነም የኢኮኖሚ ቀውሱ ተባብሶ እንደሚቀጥል መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ባለፉት ሁለት ወራት በሰሜን ጎንደር የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ራሳቸውን ያደራጁ የነጻነት ሃይሎች በገዢው ፓርቲ ተቋማት እና አባላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።
ይህንን ተከትሎ አዋጁን በኦሮምያና በአማራ ክልሎች ብቻ ተፈጻሚ እናድርገው አናድርገው በሚል ኢህአዴግ ሲመክር ቆይቶ፣ በመጨረሻም ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስኗል። ለዚህ የሰጠው ምክንያት ደግሞ በሌሎችም አካባቢዎች ያለው ህዝብ ስሜት በኦሮምያና አማራ ካለው የተለየ አይደለም የሚል ነው።