ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2009)
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሃገሪቱ ፓርላማ በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች የሴቶች ቁጥር ሁለት ሶስተኛ እንዲሆን የሚያደርግ መመሪያ ተግባራዊ ካላደረገ ፓርላማው ሊፈርስ (ሊዘጋ) እንደሚችል ረቡዕ አሳሰበ።
በሃገሪቱ ህግ መሰረት ከሁለት ሶስተኛ በላይ የሆኑ የህዝብ ተመራጮች ተመሳሳይ ጾታ እንዳይኖራቸው ቢደነግግም፣ ህጉ በኬንያ ፓርላማና በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ዘንድ ተፈጻሚ ሳይሆን መቅረቱን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
ፓርላማው የሴቶች ቁጥር በህጉ መሰረት ተግባራዊ የሚደረግበትን መመሪያ በአስቸኳይ ተግባራዊ ካላደረገ ከሁለት ወር የጊዜ ገደብ በኋላ ፓርላማው ሊዘጋ (ሊፈርስ) እንደሚችል ፍ/ቤቱ ወስኗል።
ከ349 የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት መካከል 69ኙ ብቻ ሴቶች ሲሆኑ ቁጥሩ 117 መድረስ እንዳለበት የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሳስቧል።
ሃገሪቱ በነሃሴ ወር ብሄራዊ ምርጫን ለማካሄድ እቅድ ያላት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ለምርጫው ፈተና እንደሚሆን የተለያዩ አካላት ገልጸዋል።
የኬንያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ህጉ ተግባራዊ እንዲደረግ ዘመቻን ሲያካሄዱ የቆዩ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠይቀዋል።
የሃገሪቱ ማንኛውም ህግ ተፈጻሚ ካልሆነ የኬንያ ዜጋ አቤቱታውን ለበላይ ፍርድ ቤት በማቅረብ ህግ ተፈጻሚ እንዲሆን የማድረግ መብት አለው ሲሉ የህግ ባለሙያው ጆን ማቪቶ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። ኬንያ የፓርላማ አባላቷ የተመጣጠነ የጾታ ተወካይን ካላገኙ ሃገራት መካከል አንዷ ስትሆን ከ193 ሃገራት መካከል በ100ኛ ድረጃ ላይ ተፈርጃለች።
ሩዋንዳ 61 በመቶ የሚሆኑ የፓርላማ አባላቷ ሴቶች እንዲሆኑ በማድረግ ከአፍሪካ በጥሩ ተምሳሌት ላይ ለመቀመጥ ችላለች።
547 የፓርላማ አባላት ባላት ኢትዮጵያም የሴቶች ተሳትፎ 38 በመቶ አካባቢ መሆኑን የኢንተር ፓርሊያመንት ዩኒየንን መረጃ ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ዘግቧል።
የመን፣ ኳታር፣ አማን፣ እና ሃይቲ ከሁለት በመቶ በታች የሆኑ ሴቶችን በፓርላማ በማሳተፍ ዝቅተኛና ለሴቶች መብት መከበት ትኩረት ያልሰጡ ሃገራት ተብለው ተቀምጠዋል።