መጋቢት ፳ (ሃያ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመንግስትን ድርጅቶችን ወደ ግል በማዞር ሒደት አገዛዙ ለግል ባለሃብቶች ከሸጣቸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ ከሶስት ቢሊየን ብር በላይ እንዳልተከፈለና አብዛኛውን እዳ የተሸከሙት ባለሀብቱ ሼክ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲን መሆናቸው ተገልጿል።
መንግሥታዊው አዲስዘመን ጋዜጣ በረቡዕ መጋቢት 20 ቀን ዕትሙ እንደዘገበው ከመንግሥት ወደግል ከተዛወሩ 29 ድርጅቶች በጠቅላላው ከሶስት ቢሊየን ብር በላይ ክፍያ ያልተፈጸመበት ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የሼህ አልአሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ አልከፈለም፡፡
ድርጅቶቹ ወደግል ሲዛወሩ ከመሸጫ ዋጋቸው ውስጥ 35 በመቶውን በመክፈል ቀሪውን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ የነበረባቸው ቢሆንም፣ 29 ያህል የተዛወሩ ድርጅቶች ይህን ማድረግ አልቻሉም፡፡ ዕዳ ካለባቸው ድርጅቶች መካከል ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ያልተከፈለው በሚድሮክ ኢትዮጵያ ስም ከተያዙ ስድስት ድርጅቶች ሲሆን ቀሪውን አንድ ቢሊየን ብሩ ያልከፈሉት 23 ድርጅቶች ናቸው፡፡
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ባለሃብቶቹ ያለባቸውን ዕዳ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 አጠቃለው እንዲከፍሉት ማስጠንቀቁም ታውቋል፡፡
ሼህ አልአሙዲ ባለፉት ዓመታት በፕራይቬታይዜሽን ሒደት ከ20 በላይ የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በርካሽ ዋጋ በመግዛት ቀዳሚ ሪከርድ መያዛቸው ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእጃቸው ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል በከፍተኛ ደረጃ አትራፊ የሆነው የለገደምቢ ወርቅ ማዕድን፣ ፔፕሲኮላ ፋብሪካዎች፣ ኤልፎራ አግሮ ኦንዱስትሪ፣ ጎንደር ስጋ ፋብሪካ፣ ድሬደዋ ስጋ ፋብሪካ፣ ኮምቦልቻ ስጋ ፋብሪካ፣ ጨፋ እርሻ ልማት፣ ጮራ ጋዝ (አሁኑ አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ)፣ አዲስ ጎማ ፋብሪካ (የአሁኑ ሆራይዘን ጎማ) ፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የህዝብን የልማት ድርጅቶች ወደ ግል የማዛወሩ ሂደት ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ከአገዛዙ ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች ድርጅቶችን በትውውቅ እየገዙ ይጠቀሙባቸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ጊዜ ሰማይ ለነካ የሃብት ክፍፍልና ለልዩነት መፈጠር የመንግስት የልማት ድርጅቶች ግልጽነት የጎደለው ሽያጭ አስተዋጽዎ ማድረጉ ይነገራል። አብዛኞቹ ድርጅቶች በሚድሮክና በህወሃቱ ኢፈርት የተያዙ ናቸው።