መጋቢት ፳ (ሃያ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቆራርጠው ወደ ግዛቴ ገብተዋል ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መያዙን የዚምባቡዌ የድንበር ጠባቂ ፖሊስ አስታወቀ። ቁጥራቸው 20 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በቶዮታ ፒካፕ መኪና ተጭነው ማትሳይ መንደር ውስጥ የተያዙ ሲሆን ወደ ዚምባቡዌ የሚያስገባ ማንነታቸውን የሚገልጽ ሕጋዊ ሰነዶች አለመያዛቸውንም ፖሊስ አክሎ ገልጿል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች እድሜያቸው ከ12 እስከ 18 የሚገመት ወጣቶች ሲሆኑ ከመሃከላቸው እንግሊዝኛ ቋንቋን መናገር የሚችል የለም ተብሏል። ከኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ጋር ሶስት ሾፌሮች፣ ኒውማን ኒያቲ የተባለ የ4.2 ብርጌድ የድንበር ጠባቂ ፖሊስ፣ ሕገወጥ ስደተኛ አዘዋዋሪ የሆኑ ሁለት የአገሪቱ ዜጎች እና አንድ ኢትዮጵያዊ ደላላም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች እና አብረዋቸው የተያዙት ሕገወጥ ስደተኛ አዘዋዋሪዎች የአገሪቷን የስደተኞች ሕግ አንቀጽ 29-2a በመተላለፍ ካለ ሕጋዊ ፈቃድ ወደ ዚምባቡዌ በመግባት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ኒውማን ኒያቲ የተባለው የድንበር ወታደር የ200 ዶላር መቀጮ እንዲከፍል ተደርጎ በነጻ እንዲሰናበት የተፈረደበት ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑ እና ሌሎቹ ግን እስከ ሚያዚያ 7 ድረስ በእስር ላይ እንደሚቆዩ ዚምባቡዌያን ኒውስ ኔት ዘግቧል።