መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በፊላንድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የቴንፐር ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ለአቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሊሰጥ የታሰበውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሽልማት በማውገዝ ለዩንቨርሲቲው አስተዳደር ደብዳቤ አስገብቷል።
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን አፈና፣ ድግያ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከሚዘውረው የህወሃት ኢህአዴግ ፓርቲ ባለስልጣናት ውስጥ በዋናነት በጠቅላይ ሚንስትርነት የሚመሩት አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝን በቀጣዩ ግንቦት ወር 2017 እ.ኤ.አ. ለመሸለም ማቀዱ የአካዳሚክ ተቋሙን ክብር ይነካል ብሏል መግለጫው።
ለዩንቪርሲቲው የሽልማት አዘጋጅ ፕሮፌሰር ሃኑ ኢስኮላ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ የቴንፐር ዩንቨርሲቲ ሽልማት መስጠት ከጀመረበት ከ1982 እ.ኤ.አ. ጀምሮ ባለፉት 35 ዓመታት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ነፍሰገዳይ የሆኑ ዜጎቻቸውን በጅምላ የሚጨፈጭፉ ግለሰቦችን ሸልሞ አያውቅም። ”የሕግ ልእልና የሌለባትን አገር ኢትዮጵያን ለሚመራ ሰው እንዴት ለእንደዚህ ዓይነት የክብር ሽልማት ይታጫል?” ሲሉ የኮሚኒቲው አባላት የተቃውሞ ደብዳቤ ጽፈው አስገብተዋል።
“እንደ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የመሰሉ ገዳዮችን መሸለም ገዳዮች በገዳይነታቸው እንዲቀጥሉ ከማበረታታት የዘለለ ፋይዳ የለውም” የሚለው ደብዳቤው ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ እጩ ሆኖ መቅረብ ፍትሃዊ ውሳኔ አይደለም ብሎአል።
የተቋሙን ሕግ በመጣስ የህወሃት ኢህአዲግ ስርዓትን ከዩንቨርሲቲ እስከ ክልል ፕሬዚዳንትነት፣ አሁን እስካሉበት የጠቅላይ ሚንስትር ማእረግ ድረስ ሕዝባቸውን ሲያስጨፈጭፉ ለነበሩ ካድሬ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሽልማት መስጠት በፊላንድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላትን እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር አለመስጠትን ያሳያል በማለት የኮሚኒቲው አባላት ገልጸዋል። የዩንቪርሲቲው አስተዳደር ውሳኔውን እንደገና እንዲመለከት ኮሚኒቲው ጥሪውን አቅርቧል።