ኢሳት (መጋቢት 18 ፥ 2009)
በልማት ሰበብ የዋልድባ ገዳም አይፈርስ በሚል ሲቃወሙና ድርጊቱን በመገናኛ ብዙሃን ያጋለጡት የዋልድባው መነኩሴ አባ ገብረየሱስ በመንግስት ሃይሎች ታፍነው መወሰዳቸው ተነገረ።
የዋልድባው መነኩሴ የመንግስት ስራ በማጋለጣቸው ለረጅም አመታት ከኖሩበት ገዳም እንዲወጡ ተደርጉ ከአምስት አመታት በላይ መቆሚያና መቀመጫ አጥተው ከገዳም ገዳም ሲዞሩ ቆየተዋል
አሁን ደግሞ ባለፈው ጥር 2009 አም ሱባዔ ከያዙበት ጎንደር ከሚገኝ አንድ ገዳም በመንግስት ሃይሎች ታድነው መወሰዳቸው ታውቋል።
አባ ገብረየሱስ በመንግስት ታድነው ይወሰዱ እንጂ አሁንም ያሉበትን ቦታ ለማወቅት የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት አስታውቋል። ለአፈና የዳረጋቸው ደግሞ የዋልድባ ገዳም ለልማት በሚል ሽፋን መፍረስ የለበትም በማለታቸው እንደሆነ ተገልጿል።
የዋልድባ ገዳም መነኩሴ አባ ገብረየሱስ እዚሁ ፈተና ውስጥ የገቡት ይህንኑ የመንግስት ስራ ለመገናኛ ብዙሃን ማሳወቃቸውን ተከትሎ መሆኑንም ታውቋል። ይህም የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ከመውጣት ውጭ የፈጸሙት ወንጀል ስለሌለ መንግስት በአስቸኳይ እንዲለቃቸው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
ታድነው የተወሰዱት በመንግስት ታጣቂዎች በመሆኑ በአካላቸውም ሆነ በህይወታቸው ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂው መንግስት እንደሚሆነም አመልክቷል። የዋልድባ ገዳም ያገባኛል የሚል ማንኛውም ክርስቲያን ሁሉ አባ ገብረየሱስ እንዲለቀቁ በቅዱስ ሲኖዶስ ለምዕመናንና ለተለያዩ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ማለትም አለም አቀፍ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት በማሳወቅ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፏል።
መንግስት በዋልድባ ገዳም ይዞታ ላይ የጀመረውን ስራ በአስቸኳይ እንዲያቆምና ተገቢውን መንፈሳዊ ክብር እንዲጠበቅ ተጠይቋል። ቅዱስ ሲኖዶስም አባቶች ታድነው ደብዛቸው ሲጠፋ በዝምታ መመልከት እንደሌለበትና ሁኔታውን በመከታተል ለቤተክርስቲያኒቷ ልጆች እንዲያሳውቅ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕምነት ተወካዮች አንድነት ጥሪ አቅርቧል።