ኢሳት (መጋቢት 18 ፥ 2009)
በደቡብ ሱዳን ስድስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች መገደላቸው ስጋት እንዳሳደረበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ አስታወቀ።
የእርዳታ ሰራተኞች የያዘ ተሽከርካሪ ከመዲናይቱ ጁባ ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል ወደ ምትገኘው የፒቦር ከተማ በማቅናት ላይ እንዳሉ የደፈጣ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ተወካይ የሆኑት ኡጊን አውሶ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። በደቡብ ሱዳን ከረሃብ ጋር በተገናኘ ሰዎች መሞት እንደጀመሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በአዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን የዕርስ በርስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሶስት አመት ወዲህ እንዲህ ያለ የሰብዓዊው ዕርዳታ ሰራተኞች ሲገደሉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የድርጅቱ ተወካይ አክለው አስታውቀዋል።
በሃገሪቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ እጅጉኑ ባስፈለገበት ወቅት በሰራተኞቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ስጋት ማሳደሩንም አውሶ መግለጻቸውን የደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።በተያዘው አመት በደቡብ ሱዳን 12 የእርዳታ ሰራተኞች የተገደሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የሟቾች ቁጥር 79 መድረሱም ተነግሯል።
በአዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲሁም የድርቅ አደጋ ተከትሎ 1.6 ሚሊዮን የሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ወደ ዩጋንዳ እና ጎረቤት ሱዳን እንደተሰደዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅት 4.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለከፈ የምግብ እጥረት ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚሁ መካከል 100ሺ የሚሆኑት በረሃብ ውስጥ መሆናቸውን ተመድ ይፋ አድርጓል።
እልባት ያላገኘው የደቡብ ሱዳን ግጭት ድርቁ እንዲባባስና ለሰዎች ሞት ምክንያት እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ተመድ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ዋነኛ አደራዳሪነት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የደቡብ ሱዳን መንግስትና የአማጺ ቡድኑን ለማስማማት ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ለአመታት የዘለቀው ድርድር መፍትሄ ሳያመጣ መቅረቱ ይታወሳል። በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት በአማጺ አመራሩ ላይ የጣለው የጉዞ እገዳ ድርድሩ ቀጣይ እንዳይሆን እንቅፋት መፍጠሩን ይገልጻሉ።