መጋቢት ፲፰ (አሥራ ስምንት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ቆሸ ወይም ረጲ እየተባለ በሚጠራው የአዲስ አበባ የቆሻሻ ማከማቻ አካባቢ የነበሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ማለቃቸውን ተከትሎ ፣ የመስተዳድሩ ባለስልጣናት በአካባቢው የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአፋጣኝ አካባቢውን እንዲለቁ አስጠንቅቀዋል። ነዋሪዎች እንደገለጹት የመጨረሻው የመልቀቂያ ቀን ዛሬ ነው። ምንም አይነት የሚገቡበት ቤት ሳይኖር ልቀቁ መባላቸው ድንጋጤ የፈጠረባቸው ነዋሪዎች፣ በሀዘን ላይ ሌላ ሀዘን ተደራርቦባቸዋል።
ልቀቁ መባላቸውን እንጅ ለምን እንደሚለቁ እንደማያውቁ የሚናጉት ነዋሪዎች፣ ድጋሜ ፍንዳታ ሊኖር ይችላል የሚል ቅስቀሳ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በኩል እየተሰራጨ መሆኑን ይገልጻሉ። አንዳንድ ሰዎች በፍርሃት ቢለቁም፣ ብዙዎቹ ግን የቤት ኪራይ ማግኘት እንደማይችሉ በመግለጽ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆኑም።
በቆሸ በደረሰው አደጋ ኢትዮጵያውያን ከእያቅጣጫው ገንዘብ እያዋጡ ቢሆንም፣ ገንዘቡ ለተጎጂዎች በምን መልኩ እንደሚደርስ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።