መጋቢት ፲፰ (አሥራ ስምንት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ትናንት እሁድ ምሽት ላይ አንድ የመንግስት ባለሥልጣን ያለመንጃ ፈቃድ በስካር በማሽከርከር ጋሻው የተባለ የከተማውን ወጣት ገጭቶ መግደሉን የኢሳት ወኪል ከስፍራው ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አገኘሁ ተሻገር ገሰሰ ከመጠን በላይ መጠጥ ጠጥተው ኮድ 04 የታርጋ ቁጥር አማ 04055 የሆነ የመንግስት መኪና እያሽከረከሩ ሲሄዱ ነው ከባህር ዳር ሆም ላንድ ሆቴል ፊት ለፊት ካለውና ወይን ጤና ቢሮ በር ላይ ተነስቶ ከከተማ ወደ ኤርፖርት በሚወስደው ዜብራ መንገድ ላይ ጋሻው የተባለን ወጣት የገጩት። ጠጥተው በሚያሽከረክሩት ባለሥልጣን የተገጬው ወጣት ወዲያውኑ ወደፈለገ ህይወት ሆስፒታል እንዲወሰድ ቢደረግም ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር እስከወዲያኛው አሸልቧል።
አደጋውን ያደረሱት ባለሥልጣን ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውሉም የልጁ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶችና ወዳጅ ዘመዶች በምሽት ድንገተኛ ለቅሶና ሀዘን ላይ ወድቀው በሚጯጯሁበት ወቅት ሰውየውን ይፈቱታል ወይም ሳያስሩት ያሳድሩታል የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ የተወሰኑ ሰዎች ሁኔታውን ለማዬት ወደ ጣቢያ አቅንተዋል።
ዛሬ ማለዳ ላይ አደጋው በደረሰበት ቦታ የክልሉ የወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ በርካታ ደህንነቶች መገኘታቸው ብዙዎችን ያስገረመ ሲሆን፤ ደህንነቶቹ ሕዝብ እያዬ አደጋ ካደረሰው መኪና ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ እስከ አምስት የሚደርሱ ታርጋዎችን አውጥተው መውሰዳቸውን ወኪላችን ጠቁሟል።
እንዲሁም መኪናው ወጣት ጋሻውን እግረኛ መሻገሪያ ዜብራ ላይ ከገጬ በኋላ እርዳታ ሳያደርግለት አደባባይ ጥሶ ሊያመልጥ ሲል ከግንብ ጋር ተላትሞ መቆሙን የጠቀሱት የዓይን እማኞች፤ ዛሬ ማለዳ በነበረው የትራፊክ አለካክ ወጣት ጋሻው የተገጬበትን ቦታ ወደ 50 ሜትር ራቅ አድርገው መለካታቸው አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
እስኪሰክሩ ጠጥተው፣ በዚያ ላይ መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው በመጠጥ ኃይል በማሽከርከር ልጃችንን መግደላቸው ደርብ ድርብርብ ወንጀል በሆነበት ሁኔታ አሁን ደግሞ የአደጋውን አለካክ በማሣሳት ፍትህን ለማዛባት እያደረጉት ያለው ልብን የሚያደማ ነው ያሉት የዓይን እማኞቹ፤ እየሆነብን ባለው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን ሲሉ በለቅሶ ገልጸዋል።