መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቤንሻንጉል ጉሙዝ በአሶሳ ከተማ በ7 ዓመት ወይም በ10 ዓመት አገልግሎት ከሰራዊቱ በክብር የተሰናበቱ የቀድሞ ወታደሮች ለሰላም ማስከበር ግዳጅና ለብሄራዊ ተጠባባቂ ሃይል እንዲመዘገቡ የሚጠይቁ ማስታወቂያዎች ተለጥፈዋል።
እድሜው ከ42 ዓመት በታች የሆነ ወይም የሆነች፣ በተለያዩ አግባብ ከሰራዊቱ የተሰናበተ፣ በ7 ወይም 10 ዓመት አግልግሎት ጨርሶ በክብር የተሰናበተ፣ በጸረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ ያልተሳተፈና ያልወገነ እንዲሁም በሰላም ማስከበር ተሰማርቶ ግዳጅ መጸፈም የሚያስችል ጤንነትና አካላዊ ብቃት ያለው በየቀበሌዎች እየሄደ መመዝገብ እንደሚችል በማስታወቂያው ላይ ተመልክቷል።
የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን መልሶ ለመቅጠር የተፈለገው፣ ባለፉት 2 ዓመታት አዳዲስ ምልምል የመከላከያ አባላትን ለመቅጠር የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ በመክሸፉ እንዲሁም በአገሪቱ የሚታየው የጸጥታ ችግር አድማሱን እያሰፋ በመምጣቱ መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚታየውን የሃይል ትግል ለማስቆም ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም፣ ሙከራው ውጤት አላመጣም። በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም እንዲሁም በዘረኝነትና ተስፋ በማጣት በርካታ የሚከላከያ ሰራዊት አባላት በየጊዜው ይጠፋሉ።