ኢሳት (መጋቢት 14 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ዳግም ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከተያዘው ወር ጀምሮ እስከ መስከረም ወር ድረስ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
የድርቁ አደጋ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በሚገኙት የዋርዴር እና የኮራህ ዞኖች የከፋ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ የምግብ እጥረቱ ወደ ረሃብ ደረጃ ለመሸጋጋር አንድ ደረጃ ብቻ እንደቀረው ድርጅቱ ይፋ አድጓል። ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ መገኘት ያለበት ድጋፍ በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት ተባብሱ መቀጠሉም ታውቋል።
መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሃገሪቱ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ለተጋለጡ ወደ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍን ለማቅረብ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ይሁንና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላለው የሰብዓዊ ቀውስ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱንና ችግሩ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ።
ለተረጆዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ ባለመገኘቱ ምክንያት በምግብ አቅርቦት መጠን ላይ መቀነስ እንደሚያጋጥም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች የተከሰተው የድርቅ አደጋ ለወራት የሚቀጥል በመሆኑ በተለይ በህጻናት ላይ የሚደርሰው የአካልና የጤና ችግር ሊገታ ወደማይቻል ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ ሃገሪቱ ለዳግም ድርቅ መጋለጧ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ።
ከዚህ የድርቅ አደጋ መባባስ ጋር በተገናኘ በሶማሌ ክልል በተበከለ ውሃ በትንሹ ስድስት ሰዎች መሞታቸውንና ሌሎች በርካቶች ደግሞ ለህመም መዳረጋቸውን የካቶሊክ የዕርዳታ ድርጅት ተወካዮች ረቡዕ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በጎረቤት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ራሷን እንደ ነጻ ሃገር አድርጋ ባወጀችው ሶማሊላንድ በተመሳሳይ መልኩ የተከሰተ የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ተሸጋግሮ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ይፋ ተደርጓል። በሶማሊላንድ ብቻ ባለፉት ጥቂት ቀናት አብዛኞቹ ህጻናት የሆኑ 25 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የሶማሊላንድ ሳናግ ግዛት አስተዳዳሪ አህመድ አብዲሳልይ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በሶማሊላንድና ሶማሊያ ወደ 500 ሺ የሚጠጉ ህጻናት በምግብ እጥረት ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ከመለወጡ በፊት ርብርብ መደረግ እንዳለበት የእርዳታ ተቋማት አሳስበዋል።